የገጠር ተደራሽ መንገድ የበርካቶችን የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እየፈታ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የገጠር ተደራሽ መንገድ መሠራት በርካታ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግሮቻችንን ፈቶልናል ሲሉ በሀዲያ ዞን የሶሮ ወረዳ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለህብረተሰቡ ዘላቂ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት አጎራባች አካባቢዎችን በማቆራኘት ማህበራዊ መስተጋብሮችን ከማሳለጥም ባሻገር ለዕለት ተዕለት የሰው ልጅ የህይወት ኡደት ያለው ፈይዳ የጎላ መሆኑ ተመልክቷል።

ገራድ ዮሐንስ ጎኔ፣ ዳኛ ታምራት አርፍጮና አንጃንች አበበ አቡኔ በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ የሁማሮ፣ የ2ኛ ሰልፌና የሻኖ ቀበሌያት ነዋሪዎች ሲሆኑ ከዚህ ቀደም የገጠር ተደራሽ መንገድ ባለመሰራቱ ለበርካታ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግሮች ይዳረጉ እንደነበር ገልፀው፥ የመንገዶቹ መሰራት ለችግሮቻቸው መፍትሔ እንዳስገኘላቸው ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ወራጅ ወንዞች ባሉባቸው አካባቢዎች መሻገሪያ ድልድዮች ያለመጠናቀቅና አሁን ላይ የመንገዱ ስራ የተቋረጠ መሆኑ ተግዳሮት እንደሆነባቸው አመላክተዋል።

በአሁን ጊዜ የእርሻ ስራ ግብዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን በዘላቂነት ማግኘት እንዲችሉ ባለድርሻ አካላት መፍትሔ ሊፈልጉለት እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።

በዞኑ ሶሮ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የገጠር ተደራሽ መንገድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ተረፈ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በወረዳው የተለያዩ አካባቢዎችን የሚያስተሳስሩ የገጠር ተደራሸ መንገዶች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ አበበ አክለውም ህብረተሰቡ በልማት ስራው የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀው ለመንገድ ስራው እንቅፋት የሚሆኑ ተግዳሮቶችን መቅረፍ በቅንጅት መስራትን የሚሻ መሆኑን አመላክተዋል።

የሶሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ኤርገኖ በበኩላቸው ከወረዳው የቆዳ ስፋት አንጻር ከዚህ ቀደም በርካታ የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ጥያቄዎች ከህብረተሰቡ እንደሚነሱ ጠቁመው፥ ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በተደረገው ጥረት በአሁን ጊዜ በርካታ የገጠር ተደራሽ መንገዶች እየተሰሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

በዞኑ ሶሮ ወረዳ ከግምቢቹ ሀጌ ደጌ የ10ኪ.ሜና ከግምቢቹ ሁማሮ የ34 ኪ.ሜ የገጠር ተደራሽ መንገድ በርካታ የህብረተሰቡን ችግር ያቃለሉ የመንገድ መሰረተ ልማቶች መሆናቸውንም አመላክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ እየተሰራ የሚገኘው መንገድ በማሽነሪ ብልሽት ምክንያት እንደተቋረጠ ገልፀው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ይሰራል ብለዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን