በተለያዩ ቅንጅታዊ ስራዎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መቆጣጠር መቻሉ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 09/2017ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ጊዜያት በጤናው ዘርፍ በተደረገው ጠንካራ ቅንጅታዊ ሥራ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መቆጣጠር መቻሉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የ2017 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የጤና ልማት ኢንቨስትመንት ዕቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በጂንካ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
ለመድረኩ ተሣታፊዎች መልዕክት ያስተላለፉት የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ የክልሉ ጤና ቢሮ ባለፉት ጊዜያት በዞኑ የማህበረሰቡን ጤና አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስና ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ላደረገው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበው መድረኩ የተሣካ እንድሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንደሻው ሽብሩ በ2017 በጀት አመት በቢሮው የተሠሩ ዋና ዋና ተግባራትን ጠቁመው፥ በበጀት አመቱ የወባ ወረርሽኝ በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ መታየቱን አመላክተዋል።
በተደረገው ጠንካራ ቅንጅታዊ ሥራዎች የወባ በሽታን ጨምሮ ቲቪንና ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መቆጣጠር መቻሉን አመላክተዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ላይ በበጀት አመቱ የሚስተዋለውን ውስንነት ለመቅረፍ ከጤና ቋማት ባሻገር ሁሉም የመንግስት አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በቀሪ ጊዜያት የወባና ኮሌራ በሽታን ቀድሞ የመከላከል ሥራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፥ በዚህም ሌሎች ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች በምርምር እንዲያግዙ ይደረጋል ብለዋል።
የመድኃኒት አቅርቦትና በዘርፉ ህገወጥነት ላይ የቁጥጥር ስራ በቀጣይ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አቶ እንደሻው አስታውቀዋል።
በመድረኩ የዞን ጤና መምሪያ ሥራ ኃላፊዎችና የክልሉ ጤና ቢሮ አመራርና ሠራተኞች የተሣተፉ ሲሆን፥ የቢሮው የ2017 ዓ.ም ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ቀርቦ ምክክር ይደረግበታል።
ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ከ5 መቶ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑ ተገለጸ
የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎቱን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ
የትምህርት አጀንዳ “የሁሉም ልማት በኩር አጀንዳ ነው” ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፁ