አሰቃቂ የግዲያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

አሰቃቂ የግዲያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

ሀዋሳ፡ መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሰቃቂ የግዲያ ወንጀል በፈፀመ ግለሰብ ላይ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወሰነ፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የከፍተኛ ወንጀሎች አቃቢ ህግ አቶ በያን ሞሳ እንደገለፁት ተከሳሽ አቶ መሀመድ አክመል በቀቤና ልዩ ወረዳ ሩሙጋ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጎጥ 6 ነዋሪ ሲሆን፥ ግለሰቡ መስከረም 15/2017 ዓ.ም በግምት ከረፋዱ 4:30 ሟች ሸሪፍ ኑሮ ከግል ይዞታው የዛፍ ማሳ ለአጥር ያዘጋጀውን እንጨት ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሲመጣ ሟች ራሱን መከላከል እንዳይችል መጀመሪያ በክላሽ የግራ እግሩን በመምታት፥ ኃላም ቀድሞ አዘጋጅቶት በነበረ የእንጨት መፍለጫ ፋስ ጭካኔ በተሟላበት መልኩ እጅ፣ እግሩንና ብልቱን መቆራረጡን አቃቤ ህጉ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

አደጋውን አድርሶ ከሞት ከዳነ ሊተርፍ ይችላል በሚል እሳቤ አንድ እግሩን ከቆረጠው በኃላ መሞቱን እስኪያረጋግጥ አስከሬኑን ይዞ ተሰውሮ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

ተከሳሽ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈፀም በህግ አካላት ይፈለግ እንደነበረ የገለፁት አቃቢ ህጉ፥ ሟች ካላቸው የስጋ ዝምዳናና ቅርበት የተነሳ ወንጀል እንዳይፈፅም ይገስፀው እንደነበረ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

መሰል ዘግናኝና አሰቃቂ ወንጅል በአካባቢው ያልተለመደ ነው ያሉት አቃቢ ህጉ፥ በተፈፀመው አስቃቂ ወንጀል ማህበረሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ ማዘኑን ተናግረዋል፡፡

ሟች ለማግባት 15 ቀናት ሲቀሩትና ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት የተፈፀመ ወንጀል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የልዩ ወረዳው መርማሪ ፖሊስ ምክትል ኢንስፔክተር ጀማል በደዊ በበኩላቸው፥ ወንጀለኛው ወንጀሉን ከፈፀመ በኃላ ከተሰወረበት ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጎሮ ከተማ በሰዎች ጥቆማና በክልሉና በከተማው የፀጥታ አካላት ትብብር መያዝ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ተከሳሹ በህግ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኃላ በተደጋጋሚ የቤት ጣሪያ ቀዶ ለማምለጥ መሟከሩንና በዚህም ወድቆ እንድ እግሩ መሰበሩን አስታውቀዋል ፡፡

በመሆኑም ወንጀሉ ከተፈፀመበት ዕለት ጀምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቅናጀት የወንጀሉን አፈፃፀም የሰውና የሰነድ መረጃዎችን በማደራጀት ለልዩ ወረዳው ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

ክስ የቀረበለት የልዩ ወረዳው ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተከሳሹ ወንጀሉን መፈፀሙን የሚያረጋግጡ የሠውና የሠነድ ማስረጃዎች ሲመለከት ቆይቶ መጋቢት 08/07/2017 ዓ.ም ውሳኔ ለመስጠት መያዙን ምክትል ኢንስፔክተሩ አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ በተከሰሰበት ከባድ የሠው ነብስ የማጥፋት ወንጀል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 539 (ሀ) የተመለከተውን ህግ ተላልፎ በመገኘቱ መጋቢት 8/2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት የግራ ቀኙን የቅጣት ማቅሊያ እና አስተያየት በመቀበል ተከሳሹን ያርማል ሌላውም ከመሰል የወንጀል ድርጊት እንዲርቅ ያስተምራል በማለት በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን