ሀዋሳ፡ መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከቀርከሃ አጋዥ የህክምና ቁሳቁስ መመረቱ የውጪ ምንዛሪ ከማስቀረቱም በተጨማሪ ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥር የጋሞ ዞን ደን አከባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ገለጸ፡፡
አርሶአደሩ ቀርከሃን በጥራት እንዲያመርት ሞያዊ ድጋፍ መስጠቱን የጋሞ ዞን ደን እና አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት አስታውቋል።
GIZ F4F ፕሮጀክት ከአርባምንጭ ፖሊ ሳተላይት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በቀርከሃ ስራ ለተደራጁ 4 ኢንተርፕራይዞች በህክምና አጋዥ ቁሳቁስ በማምረት ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።
በጋሞ ዞን ከ1ሺ 500 ሄክታር በላይ መሬት የቀርከሃ ሃብት ያለ ቢሆንም ከቤት ቁሳቁስ በዘለለ የማይመረት በመሆኑ በቴክኖሎጂ ሳይታገዝ ቆይቷል።
የጋሞ ዞን ደን እና አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት የብዝሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ ስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ጋንቡራ ጋንታ በአከባቢው ቀርከሃ ሲባክን እንደቆየ አስታውሰው እጸዋቱ የአከባቢ መራቆትን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚከላከል ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
ቀርከሃ የሚሰጠውን ጥቅም አርሶአደሩ ተረድቶ በጥራት በማምረት ከዘርፉ እንዲጠቀምም ሞያዊ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን አስተባባሪው አብራርተዋል።
GIZ F4F ፕሮጀክት ለጋሞ ዞን ደን እና አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ላበረከተው የአከባቢ ጥበቃ የበጀት ድጋፍ ድርጅቱን ያመሰገኑት አቶ ጋንቡራ በጫሞ ሃይቅ ተፋሰስ ዙሪያ የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ የማልማት ስራ በመሰራቱ ለወጣቱ ተጨማሪ የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።
የቀርከሃ ተዋጾ ከፍተኛ አሰልጣኝ የሆኑት አቶ አቤል ኃይለጊዮርጊስ ቀርከሃ በመጠቀም ዊልቸር በአገር ውስጥ መመረቱ በዋጋ እና ለስራ እድል ፈጠራ አበርክቶው ከፍተኛ ነው።
ስራው ዊልቸር እስከ መቶ ኪሎ የመሸከም አቅም ያለው ሲሆን 5 አመት ያለብለሽት አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ አካል ጉዳተኞች በነጻነት እንዲጠቀሙም መክረዋል።
በአርባምንጭ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የእንጨት ስራ ትምርት ክፍል አስተባባሪ እና የቀርከሃ ቴክኖሎጂ ረዳት አሰልጣኝ አቶ አንተነህ ደበበ መሰረታዊ የቀርከሃ ስልጠናው እስከ ቴክኖሎጂ ማሸጋገር የደረሰ በመሆኑ እንደ ተቋም ልምድ የተቀመረበት ነው ብለዋል።
የገረሴ አዲስ ተስፋ ቀርከሃ ማህበር አባል የሆነው ብዙነህ ሃይሌ እንደተናገረው ማህበራቸው በGIZ F4F ፕሮጀክት በኩል ባገኘው የስልጠናና የልምድ ልውውጥ ድጋፍ በቂ ክህሎት በማግኘቱ አመስግነዋል።
መንግስት የሰራላቸው የመስሪያና መሸጫ ቦታ በመፍረሱ እንዲገነባላቸው ጠይቋል።
የገረሴ ከተማ አስተዳደር ስራ እድል ፈጠራ ዩኒት ባለሞያ አቶ ያሬድ ግርማ በከተማው በሚገነባው የኮሪደር ልማት ምክንያት የፈረሰውን የመስሪያና መሸጫ ሼድ ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቀርከሃ ያመረቱትን ዊልቸር፣ ክራንች እና የሽንት ቤት መቀመጫ ናሙና ለጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አቅርበው በቀጣይ ጊዜያት በሚፈጠረው የገበያ ፍላጎት መሰረት በስፋት ለመንቀሳቀስ እየጠበቁ ይገኛሉ ።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምጭ ጣቢያችን
More Stories
ለአርሶና አርብቶ አደሮች ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሕብረተሰቡ ቀልጣፋና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን እንዲያገኝ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸው ተገለፀ
አሰቃቂ የግዲያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት