በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚስተዋለውን የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በየደረጃ የሚገኙ ባለድርሻዎች የመፍትሄ አካል ሊሆኑ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለፁ።
በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን “ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ተግባራዊ ሚና ከግጭትና ሞት አዙሪት ወደ ሁለንተናዊ ልማት” በሚል መሪ ቃል በሚዛን አማን ከተማ ሲካሄድ የነበረው የምክክር መድረክ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ የውይይትና የምክክር ሰነዱን ርዕስ መስተዳደ ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ለተሳታፊዎቹ አቀረበዋል።
በዞኑ የሚስተዋለውን የሰላምና የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በየደረጃ የሚገኙ ሁሉም አካላትና ሌሎች ባለድርሻዎች የመፍትሄ ባለቤት ሊሆኑ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በቀርበው ሰነድ ላይ በዞኑ በሱርማ፣ በቤሮ፣ በማጂ ወረዳዎችና በአጎራባች አከባቢዎች የሚስተዋሉ የዝርፊያ፣ ግድያና ጎጂ ልማዳዊ ድረጊቶች፣ ከኢንቨስትመንትና ከወርቅ ደላላዎች ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች እንዲሁም የወሰን ማስከበር ጉዳዮች ዙሪያ የውይይቱ ተሳታፊዎች በስፋት አንስተው ምክክር ተደርጎበት የጋራ መግባባት ደርሰዋል።
በምዕራብ ኦሞ ዞን ከጊዜ ወደ ጊዜ በተደረገው ውይይቶች መሻሻል መታየቱን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ገልፀው፥ የመጣው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በየደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በተገቢው ገምግመው መስራት አለባቸው ብለዋል።
ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን መመርመርና ግጭትን የማስተዳደር ጉዳይ በአመራሩ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በዞኑ ውስጥ ያሉ የወረዳዎች ችግሮችና ከአስተሳሰብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ዕጥረቶችን በአመራሩ ላይ በመስራት ችግሮቹ እንዲፈቱ እንደሚሰራ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ተናገረዋል።
በኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ በበኩላቸዉ በአካባቢው የተጀመረው የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የተጀመረውን ህግ የማስከበርና የማስፈን ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ጌታቸው ኬኒ በበኩላቸው የዞኑ አስተዳደር በአከባቢው የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች እንዲፈቱ በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር ህዝቡን በማሳተፍ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
ከክልሉ መንግስት የተቀመጠውን አቅጣጫ ወደ ታች በማውረድ ለተፈጻሚነቱ በትጋት እንደሚሰራ የጠቀሱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው ከህገወጥ ጦር መሳሪያ፣ ህገወጥ ማዕድን ምርት ዝውውር መግታት እና ሌሎች ዝርፊያ እና ግዲያ ወንጀሎች እንዲቆም በትኩረት እንደሚሰራ አሰረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በማጠቃለያቸው የእርስ በርስ ወንጀሎች፣ የአስተዳደር ወሰን፣ ከወርቅ ምረትና ግብይት በኢንቨስትመንትና የውጭ ጫናዎችን በሚመለከት የተነሱ ጉዳዮችን በጋራ ተቀናጅቶ መስራት ከሁሉም እንደሚጠብቅ አስገንዘበዋል።
በተለይ የወረዳ መዋቅሮችን በማጠናከር ከአጎራባች አከባቢ የሚመጡ ዝርፊያና ግድያዎችን በማስቆም ረገድ ህብረተሰቦቹን በጥልቀት በማወያየት እንዲሁም ወጣቶችን በተለያዩ ዘርፎች አደራጅተው ወደ ስራ በማስገባት የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚገባ ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ አስረድተዋል።
ከወርቅ ምርትና ግብይት ጋር ተያይዞ ከ70 በላይ ከተደራጁ ማህበራት መካከል 31 የሚደርሱ ችግር ያለባቸው ማህበራትን መሰረዝ መቻሉን ርዕሰ መስተዳደሩ አውስተው፥ ሁሉም ችግሮችን በጋራ በመፍታት የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ዘላቂ ሰላም ማጠናከር እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን “ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ተግባራዊ ሚና ከግጭትና ሞት አዙሪት ወደ ሁለንተናዊ ልማት” በሚል መሪ ቃል በሚዛን አማን ከተማ ሲካሄድ የነበረው የምክክር መድረክ ላይ የፌደራል የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
አሰቃቂ የግዲያ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት
ምክር ቤቶች በአገር ደረጃ የተጀመሩ የለውጥ ጉዞዎችን አጠናክርው ማስቀጠል እንደሚገባቸው ተገለጸ
ከቀርከሃ አጋዥ የህክምና ቁሳቁስ መመረቱ የውጪ ምንዛሪ ከማስቀረቱም በተጨማሪ ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገለጸ