በቤንች ሸኮ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተጀመሩ የልማትና ሰበዓዊ አገልግለቶችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

በቤንች ሸኮ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አማካኝነት የተጀመሩ ልማቶች ለማጠናከር በአባላት ማፍራት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተመላክቷል።

ከገጠር  ወደ ሚዛን አማን ከተማ ለተካለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች  በተሳትፎ የተገነቡ የንጹህ መጠጥ  ዉሃ ግንባታ  ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ  ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር የተናገሩት የዞኑ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ፍቃዱ እጀታ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፎ እየጎለበተ በመምጣቱ በአቅራቢያቸው የንጹህ  መጠጥ ውሃ ተገንብቶ ለአገልግሎት ሊበቃ ችሏል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በቀይ መስቀል የሚደረግለትን ሰበዓዊ  የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የበለጠ እንዲጠናከርም   የአባላት ማፍራት ስራ እንዲሁም የበጎ ፍቃድ የልማት ተሳትፎ  ላይ ማተኮር እንደሚገባው አቶ ፍቃዱ አሳስበዋል።    

ውሽቅን ቀበሌ አካባቢ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍ ያለ በመሆኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ   በአንድ ሳምንት ቆይታ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን አቶ ፍቃዱ ተናግረው፤ በዚህም ከ700 በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉንና ንብረቱን በሃላፊነት የቅርብ ክትትል በማድረግ እንዲጠብቁ ኮሚቴ ተዋቅሮ ባለቤት መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የውሃና ፋሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ   አቶ   ኪዳኔ ንጉሴ  በበኩላቸው፤ በተለይ በከተማ አስተዳደሩ የህዝብ  ቁጥር መጨመር  ጋር  ተያይዞ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ቢኖርም በቤንች ሸኮ ዞን ቀይ መስቀል እየተደረገ ያለውን ድጋፍ  አመስግነዋል።

በቀጣይ የአገልግሎት አድማሱን  ወደ ሌሎች አካባቢ ለማስፋት ሆነ ተከታትሎ ውሃውን ለማከም የተገልጋዮን እርካታ ለማረጋገጥ  በቅንጅት እንደሚሰራ አቶ ኪዳኔ አስረድተዋል።

የአካባቢ ነዋሪዎችም ከገጠር ወደ ከተማ ቢካለሉም ለዘመናት በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር  የቤንች  ሸኮ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስተባባሪነትና ድጋፍ ተጠቃሚ በመሆናቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የማህበሩ የአባላትን ቁጥር በማሳደግ በተለይ በሰበዓዊ አገልግሎቶች የበለጠ ተጠቃሚ  ለመሆን እንደሚተጉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከ68 ሚሊየን ብር   በላይ ወጪ G+4 የህንጻ ግንባታ ለመገንባት የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል።

በስነ-ሰርዓቱ ላይ ተገኝተው የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡትና የንጹህ የመጠጥ  ውሃ አገልግሎትን በይፋ ያስጀመሩት  የቤንች ሸኮ ዞን   ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የአስተዳዳር ጸ/ቤት ሃላፊ   አቶ እሸቱ  ሻምበል እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የቤንች ሸኮ ዞን ቅርንጫፍ  ጽ/ቤት በመንግሥት  ያልተደረሰባቸው የልማት ክፋተቶችን በማገዝ የዞኑን ህዝብ በልማትና በሰበዓዊ አገልግሎት ተጠቃሚ ሲያደርግ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በተለይ ማህበሩ ከሚሰጣቸው  ሰበዓዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ በከተማው ወቅቱ የሚጠይቀውን ዲዛይን በጠበቀ መልኩ የሚገነባው ህንጻ ለከተማዋ ገጽታ ግንባታም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው የዞኑ አስተዳደር  የተለመደውን  ድጋፍን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ማህበሩ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት አንጻርም በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች የማህበሩ አባላት ቁጥርን በማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጠው አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ ሰለሞን አበበ  – ከሚዛን ጣቢያችን