ሀዋሳ፡ መጋቢት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ የተገነቡ የመስኖ ተቋማት በአግባቡ በማስተዳደር በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የመስኖ ተቋማት ቆጠራ መረጃ ማሰባሰቢያና ማጠቃለያ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ካሳዬ ተክሌ እንዳስታወቁት፥ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች ላይ የመስኖ ተቋማት ያሉበት ደረጃ መረጃ የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል።
የመስኖ ተቋማት ቆጠራ መረጃ መሰብሰቡ በመዋቅሮች የመስኖ ተቋማት ፍትሀዊነት ለማረጋገጥና የነበሩ ችግሮችን በመለየት የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያስችል ጠቁመው፥ የመስኖ ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ በአግባቡ በማስተዳደር ተቋማቱ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ በመስኖ ተቋማት የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሀይል አማራጮችን በመጠቀም እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለስራው ትኩረት በመስጠትና ብቁ ባለሙያ በመመደብ ለመስኖ ተቋማት ስራ ውጤታማነት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ኢ/ር ካሳዬ ገልጸዋል።
በየጊዜው የሚሰጡ ስልጠናዎችን በተገቢው ስራ ላይ በማዋል እስከ ታችኛው መዋቅር ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ስራ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።
አቶ መለሰ ኃይሌ፣ አቶ አየለ ፈቀደ እና አቶ ወንድሙ ተሰማ የሀድያ፣የጉራጌ እና የከንባታ ዞኖች ውሀ ማዕድን ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊዎች ሲሆኑ አቶ ከድር ኬነሞ የማረቆ ልዩ ወረዳ ውሀ ማዕድን ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ናቸው።
ሁሉም የስራ ኃላፊዎች በሰጡት አስተያየት የተደረገው የመስኖ ተቋማት ቆጠራና መረጃ የማሰባሰብ ስራ ተገንብተው አገልግሎት የማይሰጡትን ተለይተውና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት በሙሉ አቅማችው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በክልል ደረጃ የመስኖ ተቋማት ቆጠራ መረጃ ማሰባሰቢያና ማጠቃለያ መድረክ መካሄዱ በየደረጃው የሚገኙ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት እንደሚያስችል ገልጸው፥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንሚወጡ አስረድተዋል።
በክልሉ በመስኖ ተቋማት ቆጠራና መረጃ ማሰባሰቢያ ወቅት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ በከፊል እና አገልግሎት የማይሰጡ የመስኖ ተቋማት መለየታቸውና በቀጣይም ከአገልገሎት ውጭ የሆኑ እና በከፊል አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የመስኖ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመድረኩ የክልሉ የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የዞንና የልዩ ወረዳ ውሀ ማዕድን ኢነርጂ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተካሄደ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደ ሀገር ለተጀመረው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለፀ
ሠላምን በማፅናት ስራ የመንግስታት ግንኙነት እና ሃገረ መንግስት ግንባታ ወሰኝ መሆኑ ተገለጸ