ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና አስቶንቪላ ወደ ሩብ ፍፃሜ አለፉ

ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና አስቶንቪላ ወደ ሩብ ፍፃሜ አለፉ

ሀዋሳ: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና አስቶንቪላ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል።

ሻምፒዮኑ ሪያል ማድሪድ የከተማ የባላንጣውን አትሌቲኮ ማድሪድን ከሜዳው ውጪ በመለያ ምት አሸንፎ ወደ ሩብ ፍፃሜ ተሻግሯል።

አትሌቲኮ ማድሪድ ጨዋታውን 1ለ0 በማሸነፉ ሁለቱ ክለቦች በድምር ውጤት አቻ መሆናቸውን ተከትሎ ወደ መለያ ምት አምርተዋል።

በተሰጠው የመለያ ምትም ሎስብላንኮዎቹ ኮልቾኔሮሶቹን 4ለ2 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።

የአትሌቲኮ ማድሪዱ ሁሊያን አልቫሬዝ ያስቆጠረው የመለያ ኳስ በእግሩ ሁለቴ ነክቷል በሚል በቫር ተሽሮበታል።

ሪያል ማድሪድ በሩብ ፍፃሜው ከአርሰናል ጋር የሚገናኝ ይሆናል።

በሜዳው ፒኤስቪን ያስተናገደው አርሰናል ጨዋታውን 2 አቻ ቢያጠናቅቅም በድምር ውጤት 9ለ3 ረቶ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል።

የአርሰናልን ጎሎች ዚንቼንኮ እና ራይስ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያስቆጥሩ ለፒኤስቪ ፔሪሲች እና ድሪዊች የአቻነት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።

መድፈኞቹ በቀጣይ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ከሎስ ብላንኮዎቹ ጋር ይፋለማሉ።

ከሜዳው ውጪ ሊልን የገጠመው ቦሩሲ ዶርትሙንድ 2ለ1 አሸንፎ በድምር ውጤት 3ለ2 በመርታት ወደ 8 ውስጥ አልፏል።

ለጀርመኑ ክለብ የድል ግቦችን ኤምሬ ቻን እና ባዬር ሲያስቆጥሩ ጆናታን ዳቪድ ለፈረንሳዩ ክለብ የማስተዛዘኛውን ገብ ከመረብ አሳርፏል።

ቦሩሲ ዶርትሙንድ በሩብ ፍፃሜው ከባርሴሎና ጋር የሚገናኝ ይሆናል።

አስቶንቪላ በበኩሉ በቪላ ፓርክ ለ75 ደቂቃዎች በ10 ተጫዋች የተጫወተውን ክለብ ብሩጅን 3ለ0 ረቶ በድምር ውጤት 6ለ1 አሸንፎ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተሻግሯል።

ለአስቶንቪላ የማሸነፊያ ግቦችን ማርኮ አሴንሲዮ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ኢያን ማትሰን ቀሪዋን ግብ ከመረብ ጋር አዋህዷል።

አስቶንቪላ በቀጣይ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ከፒኤስጂ ጋር ይፋለማል።

አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ በሩብ ፍፃሜው ከቀድሞ ክለባቸው ጋር የሚገናኙ ይሆናል።

ዘጋቢ: ሙሉቀን ባሳ