በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ እስኪጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የሸኮ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁ
እንደሀገር የተጀመረው የኮሪደር ልማት እስከ ወረዳ ድረስ መተግበሩ ለከተማ ውበት የጎላ ሚና እንዳለው የሸኮ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
በሸኮ ከተማ አስተዳደር ካነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ወርቁ ቦሪያብ፣ አቶ አመለ ሀይሶ፣ ቄስ ኢሳያስ ጋካና አቶ መለሰ ዳዲ በሰጡት አስተያየት፤ በሌሎች ትላልቅ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ወደ አካባቢያቸው እንዲመጣ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።
የልማቱ መምጣት የከተማን ገፅታ ከመቀየርም ባለፈ በመንገድ ጥበት ምክንያት የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ይቀንሳል ብለዋል።
በከተማው እየተጀመረ ባለው የኮሪደር ልማት የራሳቸውን ንብረት እያነሱ መሆናቸውን የከተማው ነዋሪዎች ገልፀው፤ ከልማቱ ጋር ተያይዞ የሚፈርሱ ቤቶችና የሚያርፉበትን ምቹ ሁኔታ መንግስት እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።
ከዚህ ቀደም ነባሩ መንገድ ጠባብ በመሆኑ የመኪና እና የትራፊክ አደጋዎች ይከሰቱ እንደነበር በከተማ አስተዳደሩ የ01 ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ሀብታሙ ዳዲ ገልፀው፤ ህዝቡም መንገድ ላይ ያለውን ንብረት ማንሳቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደሀገር የተጀመረው የኮሪደር ልማት በገጠር ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል መደረጉ ለከተማ ዕድገትም ሆነ ለህብረተሰብ ለውጥ ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን በከተማ አስተዳደሩ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማቴዎስ እንግሊዝ ተናግረዋል።
በከተማው በሚከናወነው የኮሪደር ልማት 14 ኪሎ ሜትር ለመስራት መታቀዱን ኃላፊው አውስተው፤ እስካሁን ባለው 8 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የማፅዳት ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከመናኸሪያ እስከ ባህል ማዕከል ያለው 1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ በ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚከናወን ያነሱት አቶ ማቴዎስ፤ በጀቱ በከተማ፣ በዞንና በክልል እንደሚሸፈን አብራርተዋል።
ከልማቱ ጋር ተያይዞ 245 ነባር ቤቶች ተለይተው ምክክር እንደሚደረግበት ኃላፊው ጠቅሰው፤ በፕላን ጥሰትና በጊዜያዊ ፈቃድ የተሰሩ ቤቶችና ኮንቴይነሮች እንደሚነሱም አመላክተዋል።
ለልማት በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን በማዋጣት በሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመሩ የኮሪደር ልማትን በማሳካት የበኩሉን እንዲወጣ አቶ ማቴዎስ አሰገንዝበዋል።
በከተማው ባለፉት 2 ዓመታት ሀዘኔ፣ ደስታዬና ሰርጌ የሚከበርው መንገድ ሲኖር ነው በሚል መሪ ቃል የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት የሸኮ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ አቶ ታምራት ምናሴ፤ የኮሪደር ልማቱ የተጀመረው ልማት እንዲጠናከር አድርጎታል ብለዋል።
በከተማው በኮሪደር ልማት ስራው የወሰን ማስከበር፣ አካባቢውን በልማትና በግለሰቦች በማስመንጠር የማፅዳት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባው አስረድተዋል።
በልማቱ በሚከናወነው የወሰን ማስከበር ስራዎች የፌደራል መንገድና የከተማ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዳሉ የገለፁት አቶ ታምራት፤ ህጋዊ ካርታና ፕላን ያላቸው ቤቶች መንግስት ካሳ ሊከፍል እንደሚችልና ህገ ወጦች እንደሚነሱም ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በአሁን ሰዓት በጉልበት እያገዘ እንደሆነና በቀጣይ በገንዘብም ድጋፍ እንደሚያደረግ ከንቲባው አውስተው፤ በትላልቅ ከተሞች ህብረተሰቡ በመዝናናት የአዕምሮ እርካታን እያገኘ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢሠራ ወረዳ ተገልጋዮች ተናገሩ
የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሰታወቀ
የሀዲያ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 24ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው