በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የውሃ አማራጮችን በተገቢው መንገድ በመጠቀም በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የውሃ አማራጮችን በተገቢው መንገድ በመጠቀም በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ባለፉት 6 ወራት በ6 አርብቶ አደር ወረዳዎች የተከናወኑ የግብርና ልማት ተግባራትና በቀጣይ 6 ወራት በሚከናወኑ መስኖ ልማት ሥራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊና የልዩ ድጋፍ ማስተባበሪያና መሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አይዴ ሎሞዶ የተከናወኑ ጅምር የመስኖ ልማት ስራዎች ካለፉት ጊዜያት የተሻሉ ቢሆንም በሂደቱ ያጋጠሙ የማሽነሪ መለዋወጫ መሣሪያዎች እጥረት፣ የነዳጅ አጠቃቀም፣ የልምድ ልውውጥ አለመኖር፣ የሀይል አማራጭ በአዋጭነት አለመተግበር፣ የበጀትና ሌሎችም ችግሮች ለአፈፃፀሙ ማነቆ መሆናቸውን አንስተዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በውይይት መድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ መንግሥት በኩል እየተደረገ ላለው ድጋፍና ክትትል አመስግነው የተሰጠው ዕድል ለዞናችን ትልቅ አቅም በመሆኑ አቅማችንን አሟጠን ልንጠቀም ይገባናል ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አክለው በዞኑ የሚገኙ የመስኖ አውታሮች በሚፈለገው ልክ በሙሉ አቅም መሥራት እንዲችሉ በመቀናጀት፣ ችግሮችን በጥልቀት በመገምገም ለቀጣይ የበልግ ሥራችን ውጤታማነት በትኩረት መሥራት እንደለበት ጠቁመው ብልሹ አሠራርን አምርሮ መታገልና በጀትን ለታለመለት ዓላማ ማዋልና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከዕቅድ እስከ ግምገማ በጋራ መሥራት ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ያዘው አፈወርቅ በበኩላቸው በመኸር ተግባራችን ካጋጠሙን ችግሮች ትምህርት በመውሰድ ለበልግ ሥራዎች በቅንጅት መሥራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ፥ በነዳጅ አጠቃቀምና የመስኖ ልማት ሥራን በባለቤትነት ከመምራት በኩል አንዳንድ ወረዳዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ማረም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ማህበረሰብ ዘንድ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆኑን ጠቁመው፥ በአፈፃፀም ሂደት የሚታዩ አቅም አሟጦ አለመጠቀም ውስንነቶችን እንዲሁም የነዳጅና ሌሎች ቁሳቁስ ችግሮችን ፕሮጀክቱ በልዩ ትኩረት እንዲቀረፍ ጠይቀዋል ።
በክልሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የአርብቶ አደር አካባቢ የመስኖ ተቋማት ጥገና አስተዳደርና አጠቃቀም ፕሮጀክት ጽ/ቤት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ የሚከናወን መሪ ዕቅድ ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ወይይት የተደረገ ሲሆን በ2017 በጀት አመት በመስኖ ለማልማት ከታቀደው 6 ሺህ 356 ሄክታር መሬት 4 ሺህ 383 ሄክታር በተለያዩ ሰብል ምርት መሸፈን መቻሉን ከቀረበው ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢሠራ ወረዳ ተገልጋዮች ተናገሩ
የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሰታወቀ
በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ እስኪጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የሸኮ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁ