ሀዋሳ፡ ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” ሲሉ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 257 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ አፈወርቅ ካሱ(ፕ/ር)፣ ዕለቱ ለተመራቂዎች የፅናት፣ የትጋትና የመስዋዕትነት ዕለት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተለይ በእንስሳት ህክምና ዶክትሬት ለመጀመሪያ ጊዜ ማስመረቅ መቻሉ የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ብሄራዊ የመውጫ ፈተና ማለፋቸው አበረታች ውጤት መሆኑን ገልጸው ስኬቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጥረት ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ለውጥ እያደረገች ስለመሆኗ ጠቁመው በዚህ ረገድ ከተመራቂ ተማሪዎች ብዙ እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት፡፡
ተመራቂዎች ባገኙት ዕውቀት ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ መክረዋል፡፡
የእውቀት ባለቤት መሆን የማህበረሰብ ኃላፊነትን መውሰድ ይጠይቃል ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤ ለሀገር ሰላም እና አንድነት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ተመራቂዎች የተቀበሉት ዲግሪ “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለተመራቂ ተማሪዎች እና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለ8ኛ ዙር በተካሄደው የምረቃ መርሃ-ግብር ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የተማሪ ወላጆች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ: ዳንኤል መኩሪያ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ የግብርና ስራዎችን ተመለከተ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለውጥ የሚበጅ፤ ዘመኑን በሚዋጅ የቴክኖሎጂ እውቀት የበለጸጉ ዜጎች የሚፈልቁበት ተቋም ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ