አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ ለ9ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን አስመረቀ
በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዶሳ ለዘጠነኛጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ለምረቃ መብቃታቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል 109 በመጀመሪያ ድግሪ ሲሆን 12 ደግሞ በሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
ካምፓሱ በ2008 ዓ.ም ወደ ስራ ከገባበት አስከአሁን በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን በመስጠት የአከባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመው፥ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ከ2 ሺ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢንጅነር አብደላ ከማል ተመራቂዎች፥ በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ በመሆን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር እራሳቸውን በማዘመን የሕዝብና የሀገር ኃላፊነትን ለመወጣት መትጋት እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ቦጋለ ፈይሳ
ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት በተሰማሩበት የስራ መስክ በተግባር በመለወጥ የአገራችን ዕድገት ማፋጠን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የትምህርት ዘርፍ ለሐገራችን ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ሊያበረክቱ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ምሩቃን የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።።
ካነጋገርናቸው ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ኤሊያስ ምስጋናው እና ቅድስት ሰለሞን በሰጡት አስተያየት በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ማህበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ለመገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል::
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ