በሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ የተመራ ልኡክ በማእከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል በቡታጀራ፣ በወራቤና በተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የመጠጥ ውሀና የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን የመስክ ምልከታ እያካሄዱ ይገኛል።
በመስክ ምልከታው አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት፤ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የድጋፍና ክትትል ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹን የሚሰሩ ተቋራጮች የህብረተሰቡን ችግር በመረዳት ፕሮጀክቶቹ ቶሎ እንዲጠናቀቁ በትጋት እየሰሩ መሆናቸው የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ሌሎችም ተቋራጮች የጀመሩትን ፕሮጀክቶች ሀላፊነት በመውሰድ አጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ክፍት ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በበኩላቸው፤ የመስክ ምልከታው በክልሉ በሳኒቴሽንና በንፁህ መጠጥ ዉሀ አቅርቦት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃን ለመገምገም አላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቡታጀራ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የሳኒቴሽን ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የፍሳሽ ማጣራት ስራውን ሲጨርስ ተረፈ ምርቱ ለግብርና ስራ ማዳበሪያነት የሚያገለግል በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ሀላፊው ጠቁመዋል።
በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ እንዲሁም በዶዮገና ከተማ የሚገነቡት የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄዎች የነበሩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዳዊት፤ ፕሮጀክቶቹ በቅርብ ጊዜ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልገሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
በቡታጀራ ከተማ የሚገነባው የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት የከተማዋን ጽዳትና ውበት ከመጠበቅ ባለፈ ፍሳሹ ከተጣራ በኋላ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል በመሆኑ ለከተማው ማህበረሰብ የስራ እድል እንደሚፈጥር የተናገሩት ደግሞ የቡታጀራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱ አህመድ ናቸው።
ፕሮጀክቱ ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እተየገነባ የሚገኝ ሲሆን ሲጠናቀቅም ለአጎራባች አካባቢዎችም በስፋት አገልግሎት እንደሚሰጥ ከንቲባው አክለዋል።
በወራቤ ከተማ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ እየተገነባ የሚገኘው የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ለህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚነት በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል ናቸው።
የመስክ ምልከታው ዛሬም የቀጠለ ሲሆን በዛሬው እለት የሆሳእና የፍሳሽ ማጣሪያ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች የሚጎበኙ ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ