የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግለት ክፍት እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እናደርጋለን – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ፡ የካቲት 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግለት ክፍት እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እናደርጋለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
129ኛውን የአድዋ ድል በዓል በተለያዩ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ በማሳለፍ ላይ የሚገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ የሞርካ ዋጫ ግርጫ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በመጎብኘት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን በሚችልበት አግባብ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዲታ ወረዳ መክረዋል።
ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማትና የብልፅግና ትልማችን ስኬት የመንገድ መሠረት ልማት ቁልፍ ሚና አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሞርካ ዋጫ ግርጫ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በግንባታ ሂደት ያጋጠሙና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተነጋግሮ በመፍታት መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በቅርቡ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በክልሉ በመገንባት ላይ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በጋራ መገምገማቸውን ተናግረው፤ የመንገድ ግንባታዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አብሮ ለመስራት ከመግባባት መደረሱን ገልፀዋል፡፡
የሞርካ ዋጫ ግርጫ መንገድ ከዚህ ቀደም እጅግ አስቸጋሪና ህብረተሰቡን ለብዙ እንግልት የዳረገ እንደነበር አስታውሰው፤ መንገዱን በመገንባት አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉት ለፌደራል መንገዶች አስተዳደር እና ለተቋራጩ ምስጋና አቅርበዋል።
በክልሉ በጥሩ ሁኔታ እየተሰሩ ያሉ መንገዶች የመኖራቸውን ያህል፤ ከካሳ አከፋፈል ጋር በተያያዘ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ ይህም መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ማነቆ እየሆነ በመምጣቱ ምክንያት አዋጅ እንዲወጣ ማስገደዱን ጭምር ተናግረዋል፡፡
73 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሞርካ ዋጫ ግርጫ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ከክልሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳሩ፤ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ያሉ ማነቆዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት በአፋጣኝ ፈትቶ መንገዱን እስከ 2018 መጨረሻ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዚህም የክልሉ መንግስት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን እንዲችል ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር አብሮ በመስራት አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይለማሪያም ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ከካሳ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመምከርና በጋራ አብሮ በመስራት መንገዱ ባፋጣኝ እንዲጠናቀቅ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንገዱ ከ7 በላይ መዋቅሮችን የሚያስተሳስር መሆኑን ገልፀው፤ የዞኑ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበርና ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ በመስራት ለፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልፀዋል።
የዲስትሪክቱ አመራሮች በበኩላቸው የተቀመጡ ማነቆዎች ከተፈቱ መንገዱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ እንደሚቻል ገልፀው፤ አሁን ባለበት ደረጃ ግንባታው 85 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የአድዋን ድል በዓል በማስመልከት ትውልዱ አንድነቱን አጠናክሮ የቀደሙ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ዘመን የማይሽረው የአድዋ ድል በልማቱ መስክ በመድገም፤ ኢኮኖሚያዊ ነፃነቷና ሁለንተናዊ ብልፅግናዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ማሻገር ይኖርበታል ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት
More Stories
የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እያካሄደ ነው
ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ ከተለመደው የመንግስት የስራ ሰዓት ውጭ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
አባቶቻችን ያስመዘገቡትን ድል ለመድገም የአሁኑ ትውልድ አንድነትን በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ተጠየቀ