የኢፌዲሪ የግብርና ሚኒስቴር ባለሙያዎች በወላይታ ዞን በዳሞት ጋሌ ወረዳ በቡጌ መስኖ ልማት የሚለማዉን የበጋ ስንዴ ጉብኝት አደረጉ
የጉብኝቱ ዓላማም የበጋ ስንዴ በተባይ እንዳይጠቃ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ባለሙያ አቶ በድሩ መሀመድ ኑር ገልጸዋል።
በ61 ሄክታር መሬት እየለማ ያለዉ የቡጌ የበጋ መስኖ ስንዴ ከተባይ ጥቃት ነፃ በመሆን በጥሩ ሁኔታ ለምርታማነት እየደረሰ መሆኑን የተለያዩ ሙያዊ ክትትል ያደረጉት አቶ በድሩ መሀመድ ኑር ተናግረዋል።
በአሁን ወቅት በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው የበጋ ስንዴ በተለያዩ ተባይ አይነቶች እንዳይወድም በመላ ሀገሪቱ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገበት መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በስንዴ ምርት እየተመዘገበ ያለው ዉጤት ኢትዮጵያ በብዙ ዶላር ከዉጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርትን በሀገር ዉስጥ ምርት ከመተካት ባለፈ ለዉጭ ገበያ በማቅረብ የዉጭ ምንዛሬ እንድታገኝም ይረዳታል ብለዋል።
ለዚህ ስኬትም በሁሉም ኢትዮጵያ ክፍሎች ያለዉ የስንዴ ምርት በተባይ እንዳይጎዳ በየመዋቅሩ ያሉ የዕፅዋት ጥበቃ ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ በቂ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉም አቶ በድሩ መሀመድ አሳስበዋል።
በወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ ማቲዎስ ጦና በበኩላቸው፤ በዞኑ በመኸርና በበጋ ወቅቶች ስንዴ በስፋት እንደሚመረት ገልፀው ምርቱ በተባይ እንዳይጎዳ የመከታተልና ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን የመርጨት ሥራ እየተሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የዳሞት ጋሌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ በለጠ በበኩላቸው፤ በቡጌ የተጀመረው ስንዴ የማምረት ሥራ በሌሎችም ቀበሌዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ብለዋል።
ከግብርና ሚኒስቴር በተሰጠዉ ድጋፍና ክትትል መደሰታቸዉን አርሶ አደሮች ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ሰላሙ ማሴቦ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ጥራቱ የተጠበቀ ከ500 ቶን በላይ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ