ስፖርት በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከማቀራረቡም በተጨማሪም ለአንድ አካባቢ ሰላም መስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ
በስምንት የተለያዩ የስፖርት ዘርፍ ለአስር ቀናት ሲደረግ የቆየው የጉራጌ ዞን የ2017 ዓ.ም የልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮናና የባህል ስፖርት ዉድድር ተጠናቋል።
የጉራጌ ዞን የ2017 ዓ.ም የልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮናና የባህል ስፖርት ዉድድር መዝጊያ ላይ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለጹት፤ ስፖርት በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከማቀራረቡም በተጨማሪም ለአንድ አካባቢ ሰላም መስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ ጤናው ተጠብቆ እንዲቆይ ስፖርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ያነሱት አቶ ላጫ መሰል ስፖርታዊ ውድድሮች ስፖርተኞች የሰሩበትን የሚያሳዩበት መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ ላይ የተጀመሩ የስፖርት የልማት ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል።
የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ረሻድ እንደገለፁት፤ መሰል ስፖርታዊ ውድድሮች በዞኑ የሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ይበልጥ እንዲቀራረቡ ይረዳል፡፡
ወጣቶች በዚህ ውድድር ተሳታፊ በመሆናቸው አምሯዊና አካላዊ ጥንካሬያቸውን የሚያጎለብት መሆኑን ሀላፊው አስረድተዋል፡፡
ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲደረግ የቆየው ሻምፒዮናው በስምንት የተለያዩ የስፖርት ዘርፍ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት እንደነበር የገለፁት ደግሞ የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትል ሀላፊና የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አደም ሽኩር ናቸው፡፡
በውድድሩ ዞኑን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞች መመልመላቸውን ያነሱት ያነሱት ሀላፊው በክልላዊ መሰል ውድድር ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡
የውድድሩ መተዳደሪያ ደንብ ተግባራዊ በማድረግ ውድድሮች መካሄዳቸውን ያነሱት ደግሞ በመምሪያው የስፖርት ውድድርና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ አብድልፈታ ናስር ሲሆኑ ስፖርተኞች መልካም ስብእና ተላብሰው ውድድራቸውን ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ውድድሩ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረ መሆኑን ያነሱት ተሳታፊዎች ለተደረገላቸው አቀባበልና ለተሰጣቸው መስተንግዶ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በውድድሩ የጉመር ወረዳ በአትሌቲክስ ጠቅላላ አሸናፊ ሲሆን በጠረጴዛ ቴኒስና በፓራ ኦሎምፒክ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሲያሸንፍ በወርልድ ቴኳንዶ የአረቅት ከተማ አስተዳደር፤ ቮሊቮል የአበሽጌ ወረዳና በባህል ስፖርት የሙህር አክሊል ወረዳ 1ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡
ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የእግር ኳስ ውድድር የፍጻሜ ጨዋታ ቀን 8 ሰአት ላይ እንደጋኝ ወረዳ ከጉንችሬ ከተማ አስተዳደር መካከል ሲደረግ እንደጋኝ ወረዳ አንድ ለዜሮ በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል።
ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ከመግፋፋት በመውጣት የመደመር ዕሳቤን በማጎልበት በህዝቦች መካከል ያሉ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስክ ያስተማራቸውን 518 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ውጤታማ የሆነ ስራ የሰራ አካባቢ ተጨማሪ ፕሮጀክት የማግኘት ዕድል አለው – ሚ/ር ዴኤታ የትምጌታ አስራት