የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን መስራት ከጀመሩ ወዲህ የአፈር ለምነት በመጨመሩ ምክንያት የሚያገኙት የሰብል ምርት ከፍ ማለቱን በሀዲያ ዞን የጎምቦራ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

በወረዳው በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስነ አካላዊና ስነ ህይወታዊ ስራዎች እንደሚለማ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በሀዲያ ዞን ጎምቦራ ወረዳ በአፈርና ዉሃ ጥበቃ ስራ ላይ እያሉ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች እንደገለጹት፤ ከባለፉት አመታት ጀምሮ በተፋሰስ ልማት ስራ እየተሳተፉ መቆየታቸውንና በሠሩት ስራም ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አካባቢያቸው ተዳፋታማ መሆኑን የገለጹት አርሶአደሮቹ ከዚህ ቀደም ለም አፈር በጎርፍ ምክንያት ታጥቦ ይወሰድ እንደነበር ጠቅሰው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ከጀመሩ ወዲህ የአፈር ለምነት በመጨመሩ የሚያገኙት የምርት መጠን ማደጉን ተናግረዋል።

ስነ አካላዊ ስራዎችን በስነ ሕይወታዊ ስራዎች ለመሸፈን ባከናወኑት ሥራም ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግሉና የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በወረዳዉ የኦርዴ ቦቢቾ ቀበሌ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ ላምባሞ እንዳሉት፤ በቀበሌዉ 575 ሄክታር መሬት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ለማልማት ከ2 ሺህ 7 መቶ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ወደ ስራው መግባት ተችሏል።

በሀዲያ ዞን የጎምቦራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ ባቾሬ በበኩላቸው በወረዳው 7 ሺህ 2 መቶ 24 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እንደሚከናወን ጠቅሰው፤ ለዚህም የሰው ጉልበትና የመሳሪያ ልየታ በማድረግ በይፋ ስራው መጀመሩንም አስረድተዋል።

ባለፉት አመታት በወረዳው በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱንም አንስተዋል።

በወረዳዉ እንደ ዘንድሮ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን የተለያዩ ችግኞችን ለማፍላት የታቀደ ሲሆን እስካሁን ከ3 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ማፍላት መቻሉንም አቶ አሰፋ ጠቁመዋል።

በወረዳው የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲጠናቀቅ የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ አሰፋ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን