ሀዋሳ፡ ጥር 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በሀድያ ዞን የጃጁራ ከተማ አስተዳደር አንዳንድ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ማራኪ ለማድረግ ከህዝቡ ጋር በመቀራረብ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
የጃጁራ ከተማ ምቹ የአየር ፀባይና የመሬት አቀማመጥ የተጎናፀፈች፣ ልማት ወዳድ ህዝብ ያቀፈችና ሰላሟም የተጠበቀ ስለመሆኗም የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ያመለክታል።
ልማቷን በማፋጠን ዕድገቷን ለማረጋገጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ሲሆን የስታዲየም ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ያነጋገርናቸው የከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ወጣት ኤልያስ ጡምጎጎ አና ዘውዲቱ ታምራት፤ የከተማው ወጣት የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የስታዲየም ዙሪያ አጥር ግንባታ በመካሄዱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ እንዲሆን ቀሪ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በከተማዋ በኢንተርፕራይዝ ማህበር ተደራጅተው የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካካል ወጣት አለሙ ቤዮሬ እና ደገፈ ኃይሌ በበኩላቸው፤ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራም ሆነ በከተማው አጠቃላይ ዕድገት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸው ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲያድግ የማምረቻና መሸጫ ቦታዎች ችግር እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
ከተማዋ ከብዙ ዓመታት በፊት ከቀበሌ መዋቅር ደረጃ ተነስታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ባሳየችው ዕድገት መነሻ ዛሬ ላይ ወደ ከተማ አስተዳደር ደረጃ እንድትደርስ የህዝቡ የልማት ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ በከተማዋ የረጅም ጊዜ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ በቆሬና ወይዘሮ ሽታዬ ሊረንሶ ናቸው።
በሁሉም መስኮች የተጀመሩ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ የልማት ተሳትፏቸውን እንደሚያስቀጥሉም ገልጸዋል።
የጃጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ለይኩን ሱልዶዕሎ እንዳሉት፤ ከተማዋ ያላትን ፀጋዎች በመጠቀም ዕድገቷን ለማፋጠን የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በግብርና ዘርፍ በተለይ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እየተሰራ ነው ያሉት ከንቲባው የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና የሌሎችም መሠረተ ልማቶች ትኩረት የተሰጠባቸው መስኮች ናቸው ብለዋል።
በወጣቱና በህዝቡ ዘንድ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የስታዲየም ግንባታ ስራ የህዝቡን ተሳትፎ መሠረት በማድረግ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው የዙሪያ አጥር ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በቀጣይ ዘመናዊ ስታዲየም ለማድረግ የታቀዱ ተግባራት ደረጃ በደረጃ እንደሚተገበሩም ከንቲባው አመላክተዋል።
የስራ አጥነትን ቁጥር ለመቀነስ በተሠራው ስራ በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት 2ሺህ 8መቶ 70 ስራ አጦችን በመለየት 1ሺህ 1መቶ 87 ወጣቶችን ከ50 በላይ በሆኑ ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም አቶ ለይኩን ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን መነሻ ያደረጉ የሰንበት ገበያዎችን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ከህዝቡ ጋር በመቀራረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለልማት ስራው መፋጠን የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ በመሆኑ “ኑ የጃጁራ ከተማን በጋራ እናልማ” የሚል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የተመዘገቡ አበረታች ዉጤቶችን በቀጣይ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ
በዳዉሮ ዞን በዘንድሮ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት 40 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ልማት መምሪያ አስታወቀ
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በመንገድ ደህንነትና ትራፊክ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ስልጠና በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ነው