የፍርድ ቤቶች እና የፍትህ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጥምረት የፍትህ አሰጣጥ ላይ ውጤታማ ማድረጉ ተገለጸ
በጥምረት መሰራቱ በሰብአዊ፣ በሴቶችና ህፃናት መብት ጥበቃ ላይ መሻሻል ማሳየቱም ተገልጿል።
በጌዴኦ ዞን ፍርድ ቤቶች እና ፍትህ ሴክተሮች በጋራ የ2018 ዓ.ም አፈፃፀም እና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ እንደገለፁት፣ ጥምረቱ የተቋቋመው በህብረተሰቡ ውስጥ የተበራከተው የስርቆት ወንጀል የዜጎችን ሰርቶ ንብረት የማፍራት መብት የሚነካ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት እና አስተማሪ ውሳኔ በመስጠት ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ነው።
ከዚህም ባሻገር ፖሊሶች፣ አቃቤ ህጎች እና ዳኞች እስከ ቀበሌ ወርደው በህብረተሰቡ ዘንድ የሚቀርበውን ክስ በማየት መረጃ እና ማስረጃ ላይ ተመስርተው ቀልጣፋ ውሳኔ በመስጠት ተጠርጣሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ከማስቀረትም በላይ የእስረኞች አያያዝን በመከታተልና ግብረመልስ በመስጠት የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል አድርገዋል ብለዋል።
የሴቶች እና ህፃናት መብት ጥሰት ወንጀሎች ሲፈፀሙ መረጃና ማስረጃን መሠረት አድርገው ቀልጣፋ ፍትህና አስተማሪ ውሳኔ በመስጠታቸው በዘርፉ የነበረውን ቅሬታ ከመፍታት አኳያም ውጤታማ መሆን ተችሏል ሲሉም አስረድተዋል።
የጌዴኦ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ዘውዴ እና የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽብሩ ሚጁ እንደገለጹት፤ በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ መልካም አስተዳደር ችግር ይነሱ የነበሩና በቀበሌያት አካባቢ የሚፈፀሙ የቡና ስርቆቶች፣ እንዲሁም በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ አስተማሪ ውሳኔ በመስጠት መከላከል ተችሏል።
የፍትህ ተግባር ከፖሊስ አንስቶ አቃቤ ህግ፣ ፍርድ ቤት እስከ ማረምያ ቤቶች ቅንጅትን የሚፈልግ ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ በዚሁ መሰረት በጋራ በትኩረት በመስራታቸው ከዓመት ዓመት ውጤታማ ለውጥ መመዝገቡን አመላክተዋል፡፡
ከ2018 ዓ.ም ትምህርት በመውሰድ በ2019 ዓመትም የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ኃላፊዎቹ አብራርተዋል።
በውይይቱ ሲሳተፉ አግኝተን ካነጋገርናቸው መካከል የይርጋጨፌ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር ቦጋለ ገመዴ እና የገደብ ከተማ ፍትህ፣ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከተማ ሞገስ እንደገለፁት፣ በ2018 ዓ.ም የፍርድ ቤቶችና የፍትህ ሴክተሮች ጥምረት ወቅቱን ያገናዘበ ክትትል እና ምርመራ በማድረግ ወንጀለኞችን ለይቶ ውሳኔ በመስጠት ረገድ ውጤታማ ነበር ብለዋል።
ይህ አሰራር ተጠርጣሪ በጅምላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ ሲንገላታ የነበረውን አሰራር ከማስቀረቱም በላይ ተገቢ መረጃና ማስረጃ የመጣባቸው ተጠርጣሪዎችን በባህላዊ ሽማግሌዎች በማስተማር ወንጀልን መከላከል ተችሏል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አብዶ አየለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
አቶ ዮሐንስ አበጋ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ
የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት ይሠራል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)