የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።



በክልሉ ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ የእርሻ ዘዴዎችን በመጠቀምና የአፈር ጤናን በመጠበቅ ምርታማነታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ቀድራላ ዋበላ (ዶ/ር)፤ ማዕከሉ የአፈር ጤናን ለመጠበቅና የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ የግብርና ምርምር አሰራሮችንና ውጤቶችን እያስተዋወቀ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የአፈር ጤናን በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግ ተግባራዊ መፍትሄዎችን ማቅረብ የግብርና ምርምር ማዕከሉ ተግባር መሆኑን የገለፁት ዶክተር ቀድራላ፤ በአካባቢው ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የአፈር ጤና አጠባበቅ ቴክኖሎጂዎችን በማጥናት፣ በማረጋገጥና ወደ አርሶ አደሮች በማስፋፋት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

የግብርና የምርምር ውጤቶች በሙከራ የእርሻ ጣቢያዎችና በአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ተቋማት ተወስነው እንዳይቀሩ ወደ አርሶ አደሮች እርሻ እንዲደርሱ የግብርና ባለሙያዎች፣ የልማት ሰራተኞችና የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።


የስልጢ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብደላ መሀመድ በበኩላቸው፤ በወረዳው የተለያዩ የአፈር ጤና አጠባበቅ ዘዴዎችን በመተግበር እንዲሁም የተለያዩ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለግብርና ስራ በማዋል የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

በአካባቢው አርሶ አደሮች ለረጅም ጊዜ ሲጠቀሙባቸው የቆዩ ባህላዊ የአፈር አጠባበቅ ልምዶች እንዳሉ የጠቆሙት ኃላፊው፤ እነዚህን እውቀቶች ከዘመናዊ የግብርና ምርምርና ቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የአፈር ጤና ሲሻሻል የሰብል እድገትና ምርታማነት ይሻሻላል ያሉት ደግሞ በስልጢ ወረዳ የሸሌዋሾ ቀበሌ የግብርና ልማት ጣቢያ ባለሙያ የሆኑት አቶ እሱባለው ታደሰ ናቸው።

የአፈር ጤናን ለመጠበቅ የሰብል ዝውውርን መተግበር፣ የሰብል ተረፈ ምርትን በእርሻ ላይ በአግባቡ መጠቀም፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም፣ አፈርን ከመሸርሸር መጠበቅ እና ተስማሚ የእርሻ አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባ ባለሙያው አስገንዝበዋል።

በወረዳው በተለያዩ ቀበሌያት ካነጋጋርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ አቡበከር መሀመድ፣ አቶ ሬድዋን ረሺድ እና ወይዘሮ ጀሚላ ሀሰን እንደገለፁት፤ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የሰብል ተረፈ ምርትን መጠቀም፣ የሰብል ዝውውርን ማካሄድ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀምና ሌሎች የአፈር ጤና አጠባበቅ ዘዴዎችን መተግበር ምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ነው።

እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ በዘርፉ የሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች በፈጠሩላቸው ግንዛቤ የአፈር ጤናን በመጠበቅና በመንከባከብ የእርሻ መሬቶች ለቀጣይ ዓመታት ምርታማ ሆነው እንዲቆዩ ያግዛቸዋል።


ዘጋቢ፦ ሀጀራ ግርማ እና ሙጂብ ጁሀር ከሆሳዕና ጣቢያችን