ልየታ በተደረገባቸው ንዑስ ተፋሰሶች 71 ሺህ 919 ሄክታር ማሳ በስነ-ሕይወታዊ ተግባራት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

ልየታ በተደረገባቸው ንዑስ ተፋሰሶች 71 ሺህ 919 ሄክታር ማሳ በስነ-ሕይወታዊ ተግባራት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ጥር 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በ289 ልየታ በተደረገባቸው ንዑስ ተፋሰሶች 71 ሺህ 919 ሄክታር ማሳ በስነ-ሕይወታዊ ተግባራት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

ዞናዊ የተፋሰስ ልማት ስራ ማስጀመሪያ መርኃ-ግብር በዞኑ ጎምቦራ ወረዳ ኦርዴ ቦቢቾ ቀበሌ ተካሂዷል።

የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ሀብታሙ ታደሰ እንደገለፁት፤ መንግስት የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች የግብናው ዘርፍ አንዱ ነው።

በዚህም የግብርና እንዱስትሪዎችን በማበልፀግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የሰብል ምርታማነትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ መፍትሔው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራ ነው ያሉት ዶክተር ሀብታሙ፤ በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በዞኑ በ289 ልየታ በተደረገባቸው ንዑሳን ተፋሰሶች 71 ሺህ 919 ሄክታር ማሳ በተለያዩ ስነ-ሕይወታዊ ተግባራት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተፋሰስ ልማት ስራው ማስጀመሪያ መርኃ-ግብር ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን እሸቱ፤ መሬት የተፈጥሮ ፀጋ በመሆኑ ልንከባከበው ይገባል ብለዋል።

በየዓመቱ በሚሰሩ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራዎች በርካታ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መምጣታቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በ1 ሺህ 301 ንዑስ ተፋሰሶች ከ1.9 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 280 ሺህ 834 ሄክታር ማሳ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አመላክተዋል።

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ታምራት አኑሎ በበኩላቸው፤ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የህብረተሰቡ የኑሮ መሰረት እንደመሆኑ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በተለየ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅ ለዚህ ሁሉ መሰረት መሆኑን አንስተዋል።

የበጋ መስኖና የሌማት ትሩፋት ስራዎች የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች እንደመሆናቸው በስነ ሕይወታዊ ተግባራት መታገዝ እንደሚኖርባቸው አንስተው ስራዎቹ በሚሰሩባቸው ቀጣይ 30 ያህል ቀናት ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተፋሰስ ልማት ስራው ማስጀመሪያ መርኃ-ግብር ወቅት ያነጋገርናቸው በዞኑ ጎምቦራ ወረዳ የኦርዴ ቦብቾ ቀበሌ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም በተሰሩ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራዎች በተለያዩ ቆላማ አካባቢዎች ሳይቀር በርካታ ለውጦች የታዩ መሆኑን ጠቁመው የተፋሰስ ልማት ስራው እስኪጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን