በኦዲት ረገድ ጠንካራና ጥራት ያለው ስራ መስራትና ብልሹ አሰራርን ማረም እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገለጸ

በኦዲት ረገድ ጠንካራና ጥራት ያለው ስራ መስራትና ብልሹ አሰራርን ማረም እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገለጸ

መስሪያ ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ 6 ወራት ዕቅድ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ የግምገማ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር አቶ አበባየሁ ኤርምያስ እንዳሉት፤ ባለፉት 6 ወራት በኦዲት ረገድ ጠንካራ ስራ እየተሰራ ቆይቷል።

በተለይም የኦዲት ሪፖርት በወቅቱ ተደራሽ ከማድረግና ለክዋኔና ለአካባቢ ኦዲት ግብረ መልስ ከመስጠት አንጻር የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ተናግረዋል።

በዚህም መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም የኦዲት ግኝት ተመሳሳይ መሆን፣ አዳዲስ የኦዲት ግኝት በአንዳንድ ተቋማት ላይ መታየት፣ ባልተሟላ ሰነድ ክፍያ መፈጸም፣ የተሰብሳቢና የተከፋይ ሂሳብ ግኝት መኖሩ በቀጣይ ሰፊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመላካች ነው ብለዋል።

እንዲሁም ከኦዲት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚታይ ውስንነትን ለመቅረፍና በነዳጅ አጠቃቀም ስርአት ረገድ የቁጥጥርና ክትትል አግባቡን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ማናጀር አቶ ታምራት ቤታ በሰጡት አስተያየት፤ የኦዲት ግኝት ድግግሞሽና ከኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች አንጻር የሚታዩ የእርምጃ አወሳሰድ ውስንነት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

በዋና ኦዲት መ/ቤት የኦዲት ቡድን አስተባባሪ ወ/ሮ ፍሬወይን ከተማ በበኩላቸው፤ ከተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ እንዲሁም የግብአት እዳ አመላለስ ጋር ተያይዞ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከተገኘው የኦዲት ግኝት ምን ያህሉ እርምጃ ተወሰደበት የሚለውን በመለየት ረገድ የተጠናከረ ተግባር ሊኖር እንደሚገባ አስተያየት የተሰጠ ሲሆን የኦዲት ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግና የአሰራር መመሪያዎችን መከተል አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የግምገማ መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የኦዲት ጥራት ስራን በአግባቡ መገምገም፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ያለው ስራ መስራትና ሌሎች ተግባራት በአግባቡ መከናወን እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን