የተፈጥሮ ሃብት የሆነውን መሬትን በአግባቡ በመጠበቅ ምርታማነትን በማሳደግ ብልፅግናን ማረጋገጥ ይገባል – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ
የተፈጥሮ ሃብት የሆነውን መሬትን በአግባቡ በመጠበቅ ምርታማነትን በማሳደግ ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ ገለፁ፡፡
ሃላፊው ይህን የገለፁት በክልሉ በቀቤና ልዩ ወረዳ የ2017 የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ እወጃ በልዩ ወረዳው በሩሙጋ ቀበሌ በተካሄደበት ወቅት ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለፁት፤ ሀገራችንን ከድህነት ማውጣት የሚቻለው የተፈጥሮ ሃብት የሆኑትን መሬት፣ ውሃ፣ የሰው ሃብት እና ጊዜን በአግባቡ አቀናጅቶ መጠቀም ሲቻል ነው፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ለግብርና ስራ ምቹ ስነ-ምህዳርና የአየር ፀባይ ያለው ነው ያሉት አቶ አብረሃም እየተሰራ ያለውን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በስነ-ህይወታዊ ስራዎች ማልማት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በልዩ ወረዳው በ23 ንኡስ ተፋሰሶች 4ሺህ 200 ሄክታር መሬት ለማልማት ግብ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል፡፡
ለዚህም አስፈለጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማጠናቀቅ ስራውን በይፋ በሩሙጋ ቀበሌ ማስጀመር መቻሉን አቶ አብድልሽኩር ገልፀዋል።
በተፋሰስ ልማት ስራው ከ25 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የልዩ ወረዳው አርሶ አደር ለተፋሰስ ልማት ስራ ያለው ተነሳሽነትና ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የልዩ ወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ምክትልና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ረሻድ አስፋው ናቸው፡፡
ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
የተፋሰስ ልማት ስራ ምንጮችና ወንዞች እንዲጎለብቱ ያስቻለ ከመሆኑም ባሻገር የተጎሳቆሉ መሬቶች ማገገማቸውና ምርታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የልዩ ወረዳው አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡ እቴነሽ ቲሬቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ ለ9ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን አስመረቀ
ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” – አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ