የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበልና የገቢ አሰባሰብ የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ

ሀዋሳ፡ ጥር 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበል የገቢ አሰባሰብ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የኣሪ ዞን አስተዳደር ልዩ አማካሪና የህዳሴው ግድብ የሀብት አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይርዳው አሽኔ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የተረጂነትና የተመፅዋችነት ታሪክ የደመሰስንበት፥ በምትኩ ወደ ታላቅነት መመለሳችንን ለአለም ህዝብ የምናበስርበት በህዝብና መንግስት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

አክለውም የግድቡ መጠናቀቅ የኃይል አቅርቦትን ከማሳደግ ባለፈ ለብልፅግና ጉዞ መሠረት መሆኑን ጠቁመው፥ እንደ ሀገር ከፍተኛ የገቢ አሰባሰብ እየተካሄደ ሲሆን፥ የኣሪ ዞን በበኩሉ ከ42 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ አስተዋዕጾ አበርክቷል።

የግድቡ ዋንጫ ለ2ኛ ጊዜ በዞኑ ለአንድ ወር በሚኖረው ቆይታ የጀመርነውን በጋራ ለመጨረስ ሁሉም የበኩሉን አሰተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፥ የህዳሴው ግድብ ሥራ ለማደናቀፍ የሚሰሩ ኃይሎችን ተቋቋሞ ለዚህ መድረሱን ብሔራዊ ኩራት እንዲሰማን ያደረገ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በብድርና ከሌሎች አጋር አካላት የሚሰሩ ብዙ ቢኖሩም ይህ ፕሮጀክት ግን በራስ አቅምና ህዝቦች ትብብር ከሀብታም እስከ ደሀ የተሳተፈበት ቃል በተግባር የተተረጎመበት ፕሮጀክትና የጋራ ሀብት መሆኑን አንስቷል።

ለውይይት የሚሆን መነሻ ሰነድ የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎችም የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶች ተሰጥቶባቸዋል።

የመድረኩ መሪዎች ከሰው ኃይል ጋር ተያይዞ የተነሱ ሃሳቦችን በቅንጅት በመፍታት ለዕቅዱ ስኬት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ከመድረኩ ጥሪ ቀርቧል።

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን