51ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባውን ከመስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ምክር ቤቱ ዛሬ በ11ኛ ቀን ውሎው በኢትዮጵያ ላይ ላይ አሳታፊ ውይይት (Interactive Dialogue) እያደረገ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንዲያጣራ የተቋቋመው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርትንም አዳምጧል።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የማደርገው ምርመራ ጊዜ ይራዘምልኝ በሚል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ጥያቄ ባቀረበበት የጄኔቫው ስብሰባ ላይ ሪፖርቱን አቅርቦ አባል አገራት ተወያይተውበታል።
በስብሰባው ላይ የተሳተፉ በርካታ ሀገራት ሪፖርቱ ገለልተኛ አይደለም እንዲሁም ፖለቲካዊ አንድምታ የያዘ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
በባለሙያዎች ኮሚሽኑ የቀረበውን የምርመራ ሪፖርት ከተቃወሙ ሀገራት መካከል፤ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ኪዩባ፣ ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ቬንዙዌላ እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ይገኙበታል።
ሩሲያ ባቀረበችው ንግግር የኮሚሽኑ ሪፖርት ፖለቲካዊ ተልዕኮ የተጫነው ነው ያለች ሲሆን÷ ቀደም ሲል በተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ለሰሩት ምርመራ እና ሪፖርት ዕውቅና እንደምትሰጥ ገልጻለች።
ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሪፖርት ሙያዊ አካሄድን ያልተከተለ መሆኑን ፖለቲካዊ ተጽዕኖም እንዳለበት ነው ያመለከተችው።
በጉባኤው ላይ የተሳተፉ በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ መፍታት እንደምትችል በማንሳት ሪፖርቱን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል።
የኮሚሽኑን ሪፖርት በጥርጣሬ ካዩት ሀገራት መካከል ዴንማርክ አንዷ ስትሆን ኮሚሽኑ ምርመራውን ሲይከናውንም ሆነ ሪፖርቱን ሲያዘጋጅ ከኢትዮጵያ እና ከክልል የስራ ሀላፊዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ግልጽ እንዲያደርግ ጠይቃለች።
ሱዳን በበኩሏ ባቀረበችው ንግግር ሪፖርቱ ቀደም ሲል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ባከናወኑት የጋራ ምርምራ እና ሪፖርት የተሸፈነ በመሆኑ የተለየ ነገር የለውም ብላለች።
የ2022 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ካውንስል የአፍሪካ አባል አገራትን በመወከል ንግግር ያደረገችው ኮትዲቯር በበኩሏ ኮሚሽኑ ከተሰጠው ሀላፊነት በላይ መሄዱን ጠቅሳ መቃወሟን ኢዜአ ዘግቧል።
የካውንስሉ የአፍሪካ አባል ሀገራት ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ኮትዲቯር፣ ኤርትራ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ሊቢያ፣ ማላዊ፣ ሞሪታኒያ፣ ናሚቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሶማሊያና ሱዳንን ያካተተ ነው፡፡
የካውንስሉ አባል አገራት በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም አካላት በአፍሪካ ህብረት በሚመራው የሰላም አማራጭ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
More Stories
የፀጥታ አካላት በየዘመኑ የአገር ክብርና ሉአላዊነትን በማረጋገጥና መስዋዕትነት በመክፈል እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ
ወባን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ ተናገሩ
በአዲሱ ዓመት የስንፍናን መንፈስ በማስወገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን አንዳለበት በዳውሮ ዞን የሚገኙ የሀይማኖት መሪዎች አሳሰቡ