ኢትዮጵያና ሩሲያ በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

ኢትዮጵያና ሩሲያ በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም በሌሎች መስኮች የሚያደርጉትን ሁሉን አቀፍ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል  ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር  ኢያቭገኒ ተርኪን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅት ዳይሬክተር ጄኔራሉ ሁለቱ ሀገራት የረጅም አመት የታሪክና የባህል ትስስር ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ወቅታዊ የኢትዮጵያን ፈተና ለማሻገር እገዛ በሚያደርጉ መስኮች ትብብራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፕሮፌሽናል ተቋም ለመገንባት እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ትብብር አቅም እንደሚፈጥርለት የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ የሁለቱ ሀገራት አጋርነት በችግር ወቅትም ተፈትኖ ፍሬያማ ስኬት የታየበት በመሆኑ በቀጣይም በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ትብብሩ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ጉዳይ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡