ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የወባ ወረርሽኝን መቆጣጠር ይገባል
ሀዋሳ፡ ሕዳር 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ፥ ክልላዊ የወባ ወረርሽኝ መቆጣጠርና መከላከል ግብረሃይል ተግባር ከክልሉ ምክር ቤት ጋር በመሆን በቦንጋ ከተማ ገምግሟል።
በክልሉ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠርና ለመከላከል ዘርፈብዙ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን በዚህም የተቀናጀ ክልላዊ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ግብረሀይል ተቋቁሞ ውጤታማ ተግባር መፈጸም መቻሉ ተነግሯል።
ክልላዊ ግብረ ሀይሉ፥ ባለፉት ጊዜያት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እስከ ቀበሌ በመውረድ ችግር ፈቺ ድጋፋዊ ክትትል ማድረግ መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም የአልጋ አጎበር አጠቃቀም ችግር፣ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎች መቀዛቀዝ፣ የመረጃ ጥራት መጓደል እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት በጉልህ የሚስተዋል ችግር መሆኑን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ከጤና ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የወባ ወረርሽኝን መቆጣጠር ተግባር መደገፍ እንደሚገባ የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች ምክር ቤቶቹ በየመዋቅሩ የጤና ተቋማት ስራ-አስፈጻሚዎች ተግባርን ተከታትለው በመገምገም መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ግብረ-መልስ መስጠት ይገባል ብለዋል።
በጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦትና ቁጥጥር ስርዓትን ማሻሻል እንደሚገባ ያስገነዘቡት የመድረኩ ተሳታፊዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም የህክምና አግልግሎት በሁሉም አካባቢ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የወባ ወረርሽኝ መከላከል ተግባርን በባለቤትነት መምራት እንደሚጠበቅባቸው ያሳሰቡት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በግብረሃይሉ ድጋፍ ወቅት የመጡ ለውጦችን ማስቀጠልና ተክተው መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በታችኛው መዋቅር ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተተክለው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ወንድሙ በሁሉም የክልሉ አካባቢ ወጥነት ባለው መልኩ የወረርሽኙ መቆጣጠር ተግባር በልዩ ትኩረት መከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
እንደሀገር የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ በክልሉ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰራ ባለው ስራ ለውጥ እየታየ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ይሁን እንጅ የወረርሽኙ ክስተት በባህሪው የሚዋዥቅ በመሆኑ ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ የመከላከል ተግባር ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ብለዋል።
ክልላዊ ግብረሃይል የወረርሽኙ መከላከልና መቆጣጠር ስራው በልዩ ትኩረት እያከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢብራሂም በአንዳንድ ጤና ተቋማትና መዋቅሮች የተንሰራፋውን ስልታዊ የወባ መድኃኒት ሌብነትና የመረጃ ጥራት መጓደል የወረርሽኝ መቆጣጠር ተግባርን እየተፈታተነ ይገኛል ብለዋል።
የመከላከልና መቆጣጠር ተግባር ውጤታማነት በዘላቂነት በማስቀጠል ወባ የክልሉ የማህበረሰብ የጤና ጠንቅ ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት የጠየቁት አቶ ኢብራሂም በዚህም የክልሉ ምክር ቤት እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍና ክትትል የሚደነቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
በህገወጥ መድኃኒት ንግድና ዝውውር ላይም ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው በዚህም የህግ የበላይነትን ለማስፈን የተጀመረው ተግባር ውጤታማ እንዲሆን የፍትህ ተቋማት ቅንጅትና ትብብር መጠናከር አለበት ብለዋል።
አቶ ኢብራሂም አክለው በሁሉም ደረጃ ወረርሽኙ ለመቆጣጠር የተጀመረው የግንዛቤ ፈጠራ፣ የአከባቢ ጥበቃ እንዲሁም ህክምናና መድኃኒት አቅርቦት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድጋፍ እንዲታከልበት በአጽንኦት ጠይቀዋል።
የየዞን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች በበኩላቸው የወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ስራውን በቁርጠኝነት ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን የክልሉ የመንግስት ከሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
More Stories
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ያለአንዳች ፀጥታ ችግር ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ የኣሪ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ማዕከል ከአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በክልሉ ከምባታ ዞን ዶዮገና ወረዳ የጀመረው የትሮፒካል የዶሮ ዝርያ ማሻሻያ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዳደረጋቸው በፕሮጀክቱ የታቀፉ አርሶ አደሮች ተናገሩ