በበጋ መስኖ የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ገለጹ

በበጋ መስኖ የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ገለጹ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ በጎጮ ቀበሌ በበጋ መስኖ የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ገለጹ።

የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት በበኩሉ በበጋ መስኖ አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት እንዲያገኝ አስፈላጊዉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በወረዳው ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ አበራ ባልቻ እንደተናገሩት በዘንድሮ በጋ መስኖ በማሳቸው ከሚመረተው የተለያዩ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ከ700 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2016 ምርት ዘመን በበጋ መስኖ 300 ሺህ ብር ወጭ አውጥተው የተለያዩ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን በማምረት ከ500 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዘንድሮ ምርት ዘመን 400 ሺህ ብር ወጭ አውጥተው 700 መቶ ሺህ ብር ያህል ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የዝናብ ወቅት ብቻ ጠብቀዉ ማረስ ብዙ ዉጤት እንደማያስገኝ ጠቁመው፥ አሁን በበጋ መስኖ እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አመላክተዋል። አሁን ላይ ከሚገኘዉ ገቢ ቤተሰባቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር መቻላቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ባለፈዉ ምርት ዘመን በወረዳዉ ዉስጥ ካሉ አርሶ አደሮች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ሞዴል አርሶ አደር በመባል ሜዳሊያ መሸለማቸዉን ተናግረዋል።

ዘንድሮ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ከወረዳዉ አልፈዉ በዞን ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን አቅደዉ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ የጎጮ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት የተፈጥሮና የእርሻ ባለሙያ በዛብህ መልካሙ በበኩላቸዉ አርሶ አደሮች የበጋ መስኖ በመጠቀም በማሳቸዉ የተለያዩ ምርቶችን እንዲያለሙ የሙያዊ ግንዛቤ እየሰጡ መቆየታቸዉን ተናግረዋል።

አሁን በበጋ መስኖ እያለሙ የሚገኙ አርሶ አደሮች የዉሃ ተደራሽነት ዉስን ከመሆኑ የተነሳ በቁጥር ጥቂት መሆናቸዉን አንስተዉ ለወደፊት በርካታ አርሶ አደሮች እንድያለሙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ም/ ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ዳዊት እንደገለጹት፤ በበጋ መስኖ አመርቂ ውጤት ለማግኘት  ታቅደዉ እየተሰራ ይገኛል።

ለዚህም አስፈላጊዉን ቅድመ ዝግጅት ጨርሰዉ ወደ ስራ እንደተገባ ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ወደ ግብ ለመድረስ ስንቀሳቀስ የተለያዩ መሰናክሎች እንደሚያገጥሙ ጠቁመዉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነዉ።

በግብርና ዘርፍ ልዩ ትኩረት በማድረግ በስፋት የሚስተዋሉ የምግብ እጥረትን በመቅረፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንዳለ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ ማቱሳል እርዳቸው – ከዋካ ጣቢያችን