በተያዘው የ2017 በጀት አመት በጉራጌ ዞን ከዋና መንገድ የማይገናኝ አንድም የገጠር ቀበሌ አይኖርም ሲሉ የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል ገለጹ
ኃላፊው ይህን ያሉት የዞኑ አስተዳደር በ2017 በጀት አመት በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከወረዳና ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ አስተባባሪ አካላት ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው።
በጉራጌ ዞን በ2016 በጀት ዓመት ክንውን ላይ የተስተዋሉ ጠንካራ ጎኖችን ወስዶ ተግባር ላይ በማዋል በ2017 በጀት አመት የታቀዱ ዋና ዋና እቅዶችን ወጤታማ በሆነ መልኩ መፈጸም እንዲቻል ከወረዳና ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ አስተባባሪ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል ውይይቱን አስመልክተው ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወልቂጤ ጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የመድረኩ ዓላማ በ2017 በጀት አመት የመንግስትና የፓርቲ ተግባራትን አጠናክሮ በመስራት የዞኑ ማህበረሰብን ብልጽግና ማረጋገጥ ሲሆን ለዚህ ስኬታማነት ደግሞ የአስተባባሪ አካላት በጥንካሬ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
በዚህም በበጀት አመቱ የሚከናወኑ ተግባራት በተጨባጭ መፈጸም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በዝርዝር ስለመታቀዱ ያነሱት ሀላፊው፤ በውይይቱ ከአስተባባሪዎች ጋርም መግባባት ላይ ተደርሷል ሲሉም ገልጸዋል።
የዞኑን ጸጋ ተጠቅሞ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጸጥታና የፖለቲካ ስራዎችን አናቦ የሚሰራ እንዲሁም በአገልጋይነትና በመርህ የሚመራ የአመራር ስርአት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላይ ይህንኑ የሚመጥኑ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመሆኑም በበጀት አመቱ የዞኑ ህብረተሰብን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሚጨበጡ ስራዎች ይሰራሉ ያሉት አቶ አለማየሁ በተለይም በተያዘው የ2017 በጀት አመት በመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ በጉራጌ ዞን ከዋና መንገድ የማይገናኝ አንድም የገጠር ቀበሌ አይኖርም ሲሉ ተናግረዋል።
ይህንኑ ወደ ውጤት ለመቀየር በዞኑ በየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች እና ተግባሩን በባለቤትነት ከሚፈጽሙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመግባባት ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት።
ሌላኛው በዞኑ ህብረተሰብ በልማት ጥያቄነት የሚነሳው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መሆኑን አስታውሰው፤ ስለሆነም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በዋናነት በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሰሩና የማይሰሩ የውሃ ቦኖዎች እና ታንከሮችን ለመለየት የውሃ ቆጠራ እንደሚካሄድ ያመላከቱ ሲሆን ይህም ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲበጅ ያስችላል ብለዋል።
የዞኑ ዋና ጸጋ የሆነውን መሬትን በመጠቀም የአርሶ አደሩን የማምረት እቅም ከፍ ለማድረግ ይተኮራል ያሉት ሃላፊው፤ በተለይም በትምህርት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በበጎ ፍቃድ እና በሌሎችም የልማት ዘርፎች ላይ አጽንኦት ሰጥቶ በመስራት ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባም ገልጸዋል።
እቅድ ብቻውን ግብ አለመሆኑንና በተለይም ብልጽግና ሰው ተኮር በመሆኑ አስተባባሪው አመራሩን፣ ማህበረሰቡንና አባላቱን በማቀናጀት እነዚህንና ሌሎች በመንግስትና በፓርቲ ደረጃ የታቀዱ እቅዶች በስኬት እንዲፈጸሙ አጽንኦት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አቶ አለማየሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ተቀራርቦ በጋራ መሥራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያዝ ተጠቆመ
የጀፎረ ባህላዊ አውራ መንገድን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተጠቆመ
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የማስተማር አቅም ግንባታ ለትምህርት ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ