የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤናን ለመጠበቅ የእናቶች ማቆያ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ

የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤናን ለመጠበቅ የእናቶች ማቆያ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ

በቢሮው የእናቶችና ህፃናት ጤናና ስርአተ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የእናቶች ማቆያ ግንባታ እድሳትና ማደራጀት ላይ ያተኮረ የአፈፃፀም ግምገማና የልምድ ልውውጥ መድረክ በጉራጌ ዞን አገና ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ፤ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ጤናን ለመጠበቅ የእናቶች ማቆያ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በእናቶች ማቆያ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎችን በሁሉም የጤና መዋቅሮች መተግበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በበኩላቸው በዞኑ ከእናቶች ማረፊያ አንጻር የተሻለ አፈፃፀም በመኖሩ እና ይህንን ተሞክሮ በሌሎችም አካባቢዎች ለማስፋት የልምድ ልውውጥ መደረጉን አብራርተዋል።

የመውለጃ ጊዜያቸው የደረሱ እናቶች ወደ ማቆያ መጥተው እንዲወልዱ በመደረጉ የእናቶች ሞትን መቀነስ መቻሉን አቶ አየለ ጠቁመዋል።

የአገና ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ግሩም መርሃባ እንደገለጹት በከተማው በሁለቱም ጤና ጣቢያዎች እንደ ሃገር በጤና ፖሊሲ የተቀመጡ መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።

በሃገሪቱ በጤናው ዘርፍ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እና የእናቶችና ህፃናትን ሞትን ለመቀነስ ግብ ተጥሎ አየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በልምድ ልውውጡ ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ የእናቶች እና ህፃናት ጤናን ለመጠበቅ የተሰራው በአገና ከተማ ጤና ጣቢያ የሚገኘው የነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያ ማዕከል ያዩትን ውጤታማ እንቅስቃሴ ተሞክሮውን ወስደው በአካባቢያቸው ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጤና ተቋሙ የእናቶች ማቆያ አግኝተን ካነጋገርናቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ማዕረግነሽ እንዳለ እና ማዕረግነሽ ወልዴ ይገኙበታል። በማቆያው በህክምና ባለሙያዎች እየተደረገላቸው ባለው እንክብካቤ መደሰታቸውን ገልፀው ከዚህ ቀደም በወሊድ ወቅት ሲያጋጥም የነበረውን የእናቶች ሞትና እንግልት ያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን