በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለፀ

በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለፀ

በተገልጋዮች አስተያየት መነሻ በየጊዜዉ የአገልግሎት አሰጣጡን እያሻሻለ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ገልጿል፡፡

ካነጋገርናቸው ተገልጋዮች መካከል አቶ ወርቅነህ ወንዴ እና አቶ ብቃሙ አርባ በጋራ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም በልዩ ወረዳ መዋቅር በነበረበት ጊዜ የህዝብ መብዛት፣ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እጥረትና መሰል ችግሮች ምክንያት አገልግሎቱን በተቀላጠፈ ሁኔታ ማግኘት ሳይችሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ግን መዋቅሮች በመከፋፈላቸውና በቂ ባለሙያዎች በመኖራቸው ያለ ምንም እንግልት አገልግሎትን በቅርበት በማግኘት ወደ ልማት ስራቸው መመለስ በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

አሁንም አልፎ አልፎ ከመዋቅራዊ ርቀት ጋር ያሉ ችግሮችና ሁሉም ጉዳዮች ካለቁ በኋላ ከውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ መጉላላቶች መስተካከል እንዳለባቸው ተገልጋዮች አሳስበዋል።

በአመያ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት ሪጅስትራር አቶ አየለ ኡቴ እንዳሉት አገልግሎቱን ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በሩቅ ላሉ የቀበሌ መዋቅሮች ድረስ በመውረድ ፍትሕ እየተሰጠ ይገኛል።

አክለውም አቶ አየለ በሩቅ ቀበሌያት የሚገኙ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ባገኙት አገልግሎት ረክተው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ለማስቻል በቅርበት ተዘዋዋሪ ችሎት የማቆም ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ በላይነሽ በየነ በበኩላቸው፤ አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትሕ ስርዓት ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በበጀት ዓመቱ በፍርድ ቤቱ ከ 800 በላይ የወንጀል መዝገቦችን በመመርመር ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ በሩብ ዓመቱ 115 መዝገቦች ተመርምረው ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል።

ተገልጋዮች ፍርድ ቤት ከመምጣታቸው አስቀድመው በባህላዊ ዘዴ በሽምግልና ጉዳያቸውን በማጠናቀቅ በፍትህ ፍለጋ የሚባክነውን ጊዜና ገንዘባቸውን በማዳን ወደ ልማት ስራቸው በመመለስ ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበው፤ ከአቅም በላይ በሆነ ጉዳይ ፍትህ በመፈለግ ወደ ፍርድ ቤት ከመጡ ግን አስፈላጊና ማሟላት የሚገባቸውን ጉዳዮች አሟልተው በመገኘት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መዘግየት እንዳይከሰት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ፕሬዝዳንቷ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ደረጀ ተፈራ – ከዋካ ጣቢያችን