የእይታ ለውጥን መነሻ አድርጎ በመስራት በዞኑ የሚገኙ ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ለውጥ መቀየር ይገባል – የጉራጌ ዞን አስተዳደር
ሀዋሳ፡ ሕዳር 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የእይታ ለውጥን መነሻ አድርጎ በመስራት በዞኑ የሚገኙ ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ለውጥ መቀየር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስገንዝቧል።
በ2017 በጀት አመት በፓርቲና በመንግስት ደረጃ በሚከናወኑ ዋና ዋና ግቦች ላይ በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ አስተባባሪ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ መድረኩ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት አመራሩ ስለሚመራው መዋቅር አሁናዊ ሁኔታዎችን በመገምገም ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚመጥኑ ስራዎች መስራት አለበት።
ዞኑ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመንግስት እና የፓርቲ ስራዎችን በመገምገም በዞኑ የተረጋጋ አመራር ለመፍጠር እየሰራ ስለመሆኑ አመላክተው በተለይም ህገወጥነትንና ኮንትሮባንድ በመከላከሉ ላይ ትኩረት መሠጠት አለበት ብለዋል።
ዞኑ የብዙ ጸጋዎች ባለቤት መሆኑን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ይህንኑ የሚመጥን የእይታ ለውጥን መነሻ አርጎ በመስራት ወደ ተጨባጭ ለውጥ መቀየር እንደሚያስፈልግና ለዚህ ደግሞ የአስተባባሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም በሃገር አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ የተቀመረበት የጉራጌ ጆፎሮን ከሌማት ትሩፋት ጋር በማስተናበር አብልጦ በመስራት የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ መለወጥ ተገቢ ነው ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በሁሉም የልማትና መልካም አስተዳደር ዘርፎች ላይ የተመዘገቡ እምርታዎችን በማስቀጠል በ2017 በጀት አመት ይበልጥ ስኬታማ ስራዎች መስራት እንዲቻል ታላሚ ያደረገ ውይይት ከአስተባባሪ አካላት ጋር መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል ናቸው።
በተያዘው በጀት አመት ዞኑን የሰላም ደሴት ከማድረግ ባለፈ የማህበረሰቡ አንድነት ይበልጥ በማጎልበት ያሉ ጸጋዎችን ተጠቅሞ ብዙ በመስራት የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማድረግ የውይይቱ አንኳር ሃሳቦች እንደነበሩም አስረድተዋል።
የዞኑን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚተገበሩ ተግባራት ላይ የሚገጥሙ ብልሹ አሰራሮችንና ህገወጥ ተግባራትን አሰራርና መመሪያን ተከትሎ መከላከል እንደሚገባና ይህንኑ ግብ እንዲመታ በተቋማት ግንባታ ላይ አትኩሮ መስራት ከአስተባባሪው ብዙ እንደሚጠበቅም ነው አቶ አለማየሁ የተናገሩት።
በመሆኑም እቅዱ መዳሰስ በሚችሉ ነባራዊ ሃቆች ላይ ተመስርቶ የታቀደ በመሆኑ አስተባባሪው በየደረጃው ያሉ አካላትን በማቀናጀት ወደ ስኬት መቀየር የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የአመራር ቅንጅትን በመፍጠር የመንግሰትንና የፓርቲ ስራዎችን መስራት የሚያስችል ወይይት መደረጉን ተናግረው በተለይም ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡን አስተባብሮ ለዜጎች ተጠቃሚነት ለመስራት እራሳቸውን ማዘጋጀታቸውም አመላክተዋል።
በውይይቱ በ2016 በተከናወኑ ዋና ዋና ተግበራት እና በ2017 በሚሰሩ ስራዎች ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ዉይይት ተካሂዷል።
ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ጤና ጣቢያው እየሰጠ ባለው አገልግሎት መደሰታቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ
የሰላምና የመከባበር ባህልን ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባ ተገለጸ