የማእድን ሀብትን በአግባቡ በማልማት ዞኑን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማእድን ሀብትን በአግባቡ በማልማት ዞኑን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በቡርጂ ዞን በማእድናት ሀብት ማልማትና እና አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የቡርጂ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኡመር ጭላሌ፤ በቡርጂ ዞን በርካታ ማዕድናት ቢኖሩም ሳይለሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በአግባቡ ከተመራ እና ከለማ ከዞኑ አልፎ ለሀገር መትረፍ የሚችል በቂ የማዕድን ሀብት አለን ሲሉም ሀላፊው አክለዋል።
በቡርጂ ዞን ደረጃ ያለውን የማእድን ሀብት እና የአጠቃቀም ስርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበት በባለሙያ ሰነድ ቀርቦ በባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዶበታል።
ውይይቱን የመሩት የቡርጂ ዞን ውሃ ማእድን እና ኢነርጂ ዩኒት መሪ አቶ አላባ ህርቦ በበኩላቸው፤ በዞኑ የሚገኙ በርካታ የግንባታ፣ የኢንዱስትሪ እና የጌጣጌጥ ማእድናትን ፍትሃዊ በሆነ አግባብ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል ዞኑ ውስጥ ያሉ የኢንዱስትሪ ማዕድናት እና የጌጣጌጥ ማዕድናትን እንዴት ማልማት እና መጠቀም እንደሚገባ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
በተለይ በከበሩ ማዕድናት አወጣጥ እና ግብይት ዙሪያ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
በዞኑ በተለይም ለግንባታ ስራ የሚውሉ ማዕድናት አጠቃቀም ዙሪያ የማህበራት፣ የባለሀብቶች እና የመንግስት ድርሻ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ማስቀረት የሚችሉ ሀሳቦች ተነስተዋል።
በቡርጂ ዞን በርካታ ማእድናት የሚገኙ ሲሆን ከግንባታ ማዕድናት ድንጋይ እና አሸዋ ከኢንዱስቲሪ ማዕድናት መዳብ፣ የድንጋይ ከሰል፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቤንቶናይት ከጌጣጌጥ ማእድናት ሳፋየር፣ ኦፓል ኤመራልድ እና የመሳሰሉ ማዕድናት ናሙናቸው ቀርቦ ምልከታ ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ፡ ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ገለጸ
የወራቤ ማረሚያ ተቋም የታራሚ አያያዝና አደረጃጀት በተገቢው መንገድ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ
ዲጂታል ኢትዮዽያን ለመፍጠር በሚሰጠው ሀገራዊ የኢ-ኮዲንግ ስልጠና ተሳትፎና ተግባራዊነት ከማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል የጉራጌ ዞን አፈፃፀም ከፊት እንደሚገኝ የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ገለፁ