የኢትዮጵያ ከፍታ

የኢትዮጵያ ከፍታ

የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ስሪት የሀገሪቱን ዜጎች በተሟላ የአስተዳደር ስርዓት ማስተናገድ አለመቻል በየጊዜው ለሚቀሰቀስ የለውጥ ናፋቂ ህዝብ የማያቧራ ትግል ምክንያት ሲሆን ይደመጣል፡፡ ከአጼው ስርዓት ጀምሮ በአገሪቱ የታየው የ1966ቱ አብዮት ህዝቦች ለገደብ የለሽ ብሔራዊ ጭቆናና ብዝበዛ የዳረጋቸውን ስርዓት ለመጣል የታገሉበት አይረሴ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ስርዓት ጅማሬ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ከ1880ዎቹ ጀምሮ ሲዋረስ የመጣው የአንድ ወገን አገዛዝ እንዲያከትም ከተደረጉ ብሔረሰባዊ ትግሎች በኋላ፥ ጭቁን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የአፄውን ግፈኛ አገዛዝ በከፍተኛ ጀግንነት ተፋልመውታል፡፡ አስከፊ ብሔራዊ ጭቆና የደረሰባቸው የሀገሪቱ ህዝቦች ያካሄዷቸው ትግሎች ብዝሃነት በአግባቡ ማስተናገድ የተሳነውን ስርዓት ለመለወጥ ያለመ ነበር፡፡

ያም ሆኖ የካቲት 1966 ዓ/ም የተቀሰቀሰው አብዮት የጭቁኑ ህዝብ ስቃይና መከራ ተባብሶ መቀጠልና የነበረው ስርዓት የህዝቦችን ብዝሃነት በአግባቡ ማስተናገድ ያልቻለ ስለነበር፥ የአጼው ስርዓት በህዝብ እምቢተኝነትና ህዝባዊ አብዮት ስልጣኑን ለደርግ እንዲያስረክብ ምክንያት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በህዝብ ኃይል የተገኘው የለውጥ ጭላንጭል የተደራጀ፥ ህዝባዊ መሰረት ያለው የፖለቲካ አደረጃጀት ሆነ መዋቅር ባለመኖሩ ወታደራዊው ደርግ በቀላሉ ስልጣኑን ጠቅልሎ ሊቆጣጠር ችሏል፡፡

የሀገሪቱ ዜጎች የናፈቁት የለውጥ ተስፋ አፍታም ሳይጓዝ በደርጉ መንግስት አምባገነናዊ ስርዓት የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰት እሮሮ በየቦታው ይሰማ ጀመር፡፡ ይህ ስርዓት ይባስ ብሎ ስራውን አብዮታዊ እርምጃ ብሎ በሚጠራው ግድያ መምራት ሲጀምር ከጭቆና ጭቆና የተፈራረቀበት ህዝብ፥ መሞት በቃኝ በማለት በሌላ የትግል ታሪክ አዲስ ስርዓት ለማዋለድ የጀመረውን ጥረት ጋሬጣ ሆነበት፤ ለውጥ የናፈቀውን ትውልድ አፍኖ ፀጥ አደረገው፡፡ በየሥርቻውና በየጥጋጥጉ በጥይት እየደፋ ሬሳውን ቀባሪ አሳጣው፡፡

ምንም እንኳ በደርግ ዘመን ፊውዳላዊ መሠረት ቢናድም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ብዝሃነትን በአንድ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ገዢ ሥርዓት ተምሳሌት በተቀረጸ ኢትዮጵያዊነት ለመተካት የተደረገ ሙከራ፥ በሥነ-ሶሻሊዝም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ያም ሆኖ ጭቆናና ሞት ያስመረረው ህዝብ ግንቦት በ1983 ዓ.ም፥ ከ 17 ዓመታት በኋላ የብዙ ሺህ ኢትዮጵውያንን መስዋዕትነትን በጠየቀ ትግል በኢህአዴግ መሪነት የአምባገነናዊው ደርግ ስርዓት ግብአተ መሬት ተፈጸመ፡፡

የኢህአዴግ መንግስት የብሔር ብሔረሰቦችን መብትና የእኩልነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ቢችልም፥ ቅሉ ግን በሁለቱም የስርዓት ለውጥ ውስጥ የዜጎችን ዲሞክራሲ ያላገናዘበና በከፍተኛ ደረጃ የሰብአዊ መብቶችን የጣሰ በመሆኑ የሀገሪቱን ህዝቦች ለዳግም ለውጥ ፍለጋ እንዲንቀሳቀሱ አስገደደ፡፡

በህዝብ እምቢተኝነት ማዕበል የተፈተነው ኢሕአዴግ “ራሴን በጥልቅ አድሻለሁ“ ቢልም የጭቆና ቀንበር ያንገሸገሸውና የስርዓት ለውጥ የሻተ ህዝባዊ ተቃውሞ በመላ አገሪቷ እየሰፋ፣ የለውጡን አይቀሬት የተረዱ የፓርቲው አመራሮችም የህዝቡን ስሜት አጢነው ለውጡን አቀናጅተው እንዲመሩ ኃላፊነት ወደቀባቸው፡፡

ግንባሩ በነበረበት የአወቃቀር ችግር ወጥ የሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ግቡን በተሟላ ሁኔታ ማሳካት አልቻለም፡፡ የአጋር ፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራቸው ጉዳይ በጋራ የመወሰን መብት ማጣትና እውነተኛ የፌደራሊዝም ስርዓት መተግበር አለመቻሉ ሌላው ፈታኝ ጉዳይ ነበር፡፡ የ“እኔ አውቅልሃለሁ” አካሄድ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የለውጥ ፍላጎት እንዲቀጣጠል ገፊ ምክንያት ሆነ፡፡

ጭቆናና የግፍ አገዛዝ ያንገሸገሸው ህዝብ ግን ውሎ አድሮ ስርዓቱን ገርስሶ ነጻነቱን ለመቀዳጀት ተነሳ። ግንባሩን ለጠበንጃ ሰጥቶ፣ በእልህ አስጨራሽ ትንቅንቅና እምቢተኝነት ስርዓቱን መገዳደር ቀጠለ።

በአራት እህት ድርጅቶች የተዋቀረው ገዢው ፓርቲ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ቢያወጣም የስርዓት ለውጥ የሻተው ህዝባዊ ተቃውሞ በመላ አገሪቷ መቀጣጠሉን ተከትሎ መፍትሔው ፖለቲካዊ ውሳኔና ድርድር በመሆኑ የሀገሪቱን ገዢ ፓርቲ የበረታ ጫና ውስጥ ከተተው፡፡
በሀገሪቱ የታየው እልህ አስጨራሽ የትግል ጉዞ፥ ከባድ የፖለቲካ ቀውስ እንዲፈጥር ከማድረጉም በላይ የኢህአዴግን የግንባር ህልውና ያከሰመ ህዝባዊ ማዕበል የለውጡን አይቀሬነት አበሰረ፡፡

ይህን ተከትሎ; ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የህዝብ ተቃውሞ ሊቀለብስ ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ፥ ዶክተር ዐቢይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።

የድርጅቱ ውሳኔ እጅግ ፈጣንና ስር-ነቀል ለውጥ በፓርቲው ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ፥ በ1996 ዓ.ም ከ5ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ጀምሮ የኢህአዴግ ምክር ቤት ውህደትን ለማከናወን ሲያስተላልፍ የነበረው ውሳኔ ተግባራዊ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችል እንቅስቃሴ አደረገ፡፡ በወቅቱ የኢህአዴግ ምክር ቤት ውህደትን ለማከናወን ውሳኔውን ሲያሳልፍ ከአራቱ አባል ድርጅቶች አንዱና የግንባሩ መስራች የነበረው ከሕወሃት በስተቀር ቀሪዎቹ ውህደቱን ፈጸሙ።

ውህደቱ የሶስቱ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለ27 ዓመታት በአጋርነት ስም እንደ ሶስተኛ ወገን ተቆጥረው በአገሪቱ ማህበረ-ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ዕድል ተነፍጓቸው የነበሩ የየክልሉ ገዥ ፓርቲዎች ያካተተ ነበር።

ሕግና ስርዓትን ተከትሎ የተመሰረተው አዲሱ ውህድ ፓርቲ ‘ብልጽግና’ በሚል ስያሜ ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም በኢሕአዴግ ምክር ቤት መጽደቁ ይፋ መሆኑን ተከትሎ፥ ይህ እንዲሆን ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎች በሀገሪቷ የናፈቁት ለውጥ ሀዲዱን እንደያዘ አመኑ፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ተችሯቸው የለውጥ ስራቸውን ጀመሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ፥ አገራዊ ለውጡ መሰረት እንዲይዝ የሚያስችሉ ተቋማዊና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማከናወናቸውን ተከትሎ፥ ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባህል፣ በብዝሀነት እና በስልጣኔ የነበራትን ቀደምት ክብርና ከፍታ በወንድማማችነትና ትብብር ላይ በተመሰረተ መርሆ ለመመለስ የጀመሩት ስራ የብዙሃኑን ቀልብ ሳበ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያውያን የለውጥ ፍላጎትና ንቅናቄ የተወለደው ብልጽግና ፓርቲ፥ የዲሞክራሲ፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የእኩልነት ጥያቄዎችን ይዞ፥ ለውጡን ለመምራት እድል ያገኘ ህብረ-ብሔራዊ፣ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ከተመሠረተ 5ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው፡፡

ምንም እንኳ የብልጽግና ፓርቲ ከጅምሩ የተለያዩ ፈተናዎች ያልተለዩት ቢሆንም የለውጡ አመራር በነበረው ቁርጠኝነት፥ ያጋጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ መልከ ብዙ ጫና ሳይበገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መስኮች ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

አገሪቷ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የውጭ ታዛቢዎች በፍትሃዊነትና ገለልተኛነቱ የመሰከሩለት፣ ኢትዮጵያዊያን በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን የሰጡበት 6ኛው ዙር አገራዊ ምርጫም በስኬት ተከወነ። ኢሕአዴግን አፍርሶ በአዲስ ውህደት የተመሰረተው ብልጽግና ፓርቲም በምርጫው አሸናፊ ሆነ።

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ፥ ለህዝቦች የዘመናት ጥያቄ አማራጭ የአስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ በማድረግ እንደየ አከባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ የተለያዩ የመዋቅር ክለሳ በማድረግ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህብራዊ፣ ፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት ተደረገ፡፡

በተለይ በሀገራችን ለውጡን ተከትሎ ከ56 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሄረሰቦችን በአንድነት ይዞ የነበረው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የዞን መዋቅሮች፥ የራስን ዕድል በራስ የማስተዳደርና በክልል የመደራጀት ጥያቄያ ጎልቶ የወጣበትና በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47 መሠረት የመደራጀት መብታቸው ምላሽ እንዲያገኝ የተሄደበት ርቀት ተጠቃሽ የለውጡ ትሩፋት ነው፡፡

በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በመንግስት አስፈጻሚነት፥ የዜጎችን ጥያቄ በአንድ ጀምበር መፍታትና በ‘ጊዜ የለንም’ መንፈስ መስራት፥ የአንድ ህዝባዊ መንግስት ተቀዳሚ ተልዕኮ ቢሆንም፤ ይህ ግን በባህሪይው የተለየና የዜጎችን ተባባሪነት ብሎም ባለድርሻ ማድረግ የሚጠይቅ ነበረ፡፡
በዚህም መንግስት ህዝቡን በማሳተፍና በማስተባበር በርካታ ጉዳዮችን ማሳካት ችሏል፡፡

ምንም እንኳ ሀገሪቱ ከተመሠረተ ገና 5 አመት በሆነው መሪ ፓርቲ ብትመራም፥ በሰላምና ጸጥታ፣ የተለያዩ ሪፎርሞችን በማካሔድ አዳዲስ ተቋማትና መዋቅሮችን ማጽናት፣ በልማትና መልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች፥ መንግስት ሆነ ፓርቲው ሰው ተኮር ለመሆናቸው በለውጡ የተገኙ ስኬቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡

በምጣኔ ሃብት ረገድ የኢትዮጵያዊያን የሰንደቅ-ዓላማ ፕሮጀክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውስብስብ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለአቅመ ሃይል ማመንጨት እንዲበቃ የፓርቲው የመሪነት ሚናና ያልተቋረጠ ድጋፍ ለተመዘገበው ውጤት የነበረው አበርክቶ ከፍተኛ ነው፡፡

የሃሳብ ልዕልና የገለጠው አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት፣ በገበታ ለሸገር፣ በወዳጅነት አደባባይ ግንባታ፣ በእንጦጦና አንድነት ፓርክ፣ በሀላላ ኬላ፣ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ጨበራ ጮርጮራ በአስደናቂ ፍጥነት የተመረቁ ናቸው፡፡ በገበታ ለአገር የታቀፉ ፕሮጀክቶች ክዋኔ፥ በአዳዲስ የአመራር ዘይቤ “ጀምሮ የመጨረስ” አቅም የታየባቸው፤ በሀሳብ ልዕልና የተመራ የቤቶችና የከተማ መሠረተ ልማት፣ የአዲስ አበባና የክልሎች የኮሪደር ልማት ሀገር የሚያሻግሩ የፓርቲው ውጥኖች ናቸው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር የተያዙ የልማት ግቦች እንዲሳኩ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ የሚተገበሩ እቅዶችን ከግብ ለማድረስ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስክ ሰፋፊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ግንባታዎች እውን እንዲሆኑ አድርጓል።

በፖለቲካና ሀገረ-መንግስት የማፅናት ስራ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች ቢመዘገቡም ዳሩ ዛሬም ኢትዮጵያ ከመልከ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች አልተላቀቀችም። ጽንፈኝነት፣ ነጠላ ትርክት፣ የተዛቡ ትርክቶች ጥለውት ያለፉት ጠባሳ፣ ጦርነት ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና በእድገት ጉዞ ውስጥ የሚታዩ ፈተናዎች ቢኖሩትም በበርካታ ስኬቶች ታጅቦ 5ኛ ዓመት በዓሉን ‹‹የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል እያከበረ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ መንበረ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው የሚያቀነቅኑት አገርን በጽኑ መሰረት ላይ የማንበር ግብ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። የተስተካከለ የፖለቲካ ስርዓትን መዘርጋት፣ በህብረ ብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ስርዓት መፍጠር፣ ብዝሃነት የግጭትና የፉክክር ሳይሆን ጌጥና የአብሮነት መገለጫ የሆነበት ማህበረ-ኢኮኖሚ በመገንባት ዜጎችን ወደ ከፍታ ማሸጋገር ይገባል።

የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ማጎልበት፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስተጋብር ማስቀጠል፣ በታሪክ መወራረስ እርሾን የነገ አብሮነት እሴትነት መጠቀም፣ የጥል ግድግዳን አፍርሶ የፍቅር ድልደይ መገንባት፣ ዘላቂ ህዝባዊ ተግባቦትን ማጠናከር ያሻል።

ኢትዮጵያ በምታካሂደው አገራዊ ምክክር መድረክ የሀሳብ ልዕልና ለጽኑ አገረ-መንግስት ግንባታ እምርታ እንዲመዘገብ ያሉንን እሴቶች ተጠቅሞ ውጤታማ አገራዊ መግባባት የመፍጠር፣ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሰፈነባት አገር መገንባት የወቅቱ ጥያቄ ነው። ለነዚህ ግቦች እውን መሆን የገዥው ፓርቲ ብልጽግና ሃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ ውስጣዊና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ተራማጅ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ምቹ መደላድል መፍጠር አስፈላጊ ነው።

የብዝሃ ልሳን፣ የቱባ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት እና የሕብረ ብሔራዊነት ካስማ፣ ከዳሎል እስከ ራስ ደጀን አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ ድንቅ ተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤቷ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ትሻለች። ፀጋዎቿን አልምታ ዜጎቿን ፍሬ ማቋደስ፣ በድህነት አረንቋ የሚማቅቁ ዜጎቿን ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ መለወጥ የመንግስት ሃላፊነት ነው፤ የወቅቱ መንግስት ደግሞ ብልጽግና ነው።

በተለይ ከፍተኛ የእርሻ መሬት፣ በአዎንታዊ ሁኔታ እያደገ የመጣ የሰው ሀብት፣ ንጹህ የውሃ ክምችት፣ ማዕድን፣ ኢነርጂና ፋይናንስ የኢትዮጵያ የመበልጸግ ጥሪትና አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል ከቻለ በእርግጥም ብልጽግናን ማረጋገጥ የሩቅ ህልም አይሆንም፡፡

ግብርናውን በማዘመን በ10 ለ10 ኢኒሼቲቭ፣ በሀገር አቀፍ የስንዴ ኢኒሼቲቭ፣ የክላስተር እርሻ፣ የግብርና መካናይዜሽን፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራን ተግባራዊ በማድረግ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሀገሪቷን አርሶ አደር ኑሮ በማሻሻል አገራዊ ፖሊሲዎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘገቡ መስራት ይጠይቃል፡፡

የሀሳብ ልዕልና የገለጠውን ጭስ አልባ ኢንዳስትሪ የቱሪዝም መስክ ማልማትና ማስተዋወቅ አገራዊ ገቢን ለማሳደግ ብርቱ ስራ ይጠይቃል። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ መስህቦችን የታደለች የቱሪዝም አቅም ያላት ሀገር ነች፡፡ ከዲፕሎማቲክ ተቋማት መቀመጫ መሆናችን ጋር ሲደመር ተጨማሪ አቅም ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ዝርዝር የቱሪዝም አቅም እና ተያያዥ እድሎች በጥናት የተለየ በመሆኑ፥ ይህንን በግብኣትነት ወስዶ ልማት ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡

የአምራች ዘርፉ እምርታዊ እድገት አስመዝግቦ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በማፋጠን፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማትና የፕሮጀክቶች ማኔጅመንት አቅምን ማጎልበት እና ሌሎችም አይነት የዘላቂ ልማት ግቦችን መሬት ላይ ማውረድ ተገቢነቱ አያጠያይቅም።

የማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ እስከ 2018 ድረስ ዝቅተኛ ደረጃና ለአጠቃላይ ጥቅል የሀገር ውስጥ ልማት ከ6 በመቶ በላይ አስተዋዕጾ ማበርከት ሳይችል ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከለውጡ ወዲህ በሪፎርሙ በ2020 ዘርፉ ከአጠቃላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 60 በመቶ እንዲሸፍን በማድረግ ከ230ሺህ በላይ አዳዲስ የስራ እድሎች መፍጠር ተችሏል፡፡

ካፒታልና ገቢን በማሻሻል በ2018 ከነበረው ካፒታል 4 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር በ2021 ወደ 5 ነጥብ 12 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፥ የተገኘው ገቢ በ2018/19 ከነበረው 453 ሚሊዮን ዶላር በ2020/21 ወደ 495 ሚሊዮን ዶላር ማሳደግ ተችሏል፡፡

ብሔራዊ የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ በማዘጋጀት እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች በመደረጉ ስኬት የተመዘገበ ሲሆን፥ ከኢንደስትሪ ፓርኮች ብቻ በነበረው ኤክስፖርት በ 2019/20 የተጣራ 165 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡ በነዚሁ ፓርኮች በ2019 እና 2022 መካከል 600 ሚሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶች መገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የሃሳብ ልዕልና ለዲፕሎማሲው ከፍታ መጠበቅና የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ጎረቤት ተኮር ስልት ማተኮር ይገባል፡፡ ኢ-ተገማች በሆነው የዓለም ኅይላት አሰላለፍ ባለበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ብልጠትና ብልሃት የተሞላበት አረማምድ ያሻታል።

ለዚህ ደግሞ ለሙያው ብቃትና ዕውቀት መርህ ላይ የተመሰረተ፣ የየወቅቱን የዓለምን አዝማሚያ ተንትኖ የሚሰራ አደረጃጀትና አሰራር መዘርጋት ይጠይቃል። የኢትዮጵያን እጅ በመጠምዘዝ ሀብቶቿን ተጠቅማ እንዳትበለጸግ የሚደረጉ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫናዎችን ተቋቁሞ የውጭ ሃይላትን ፍላጎቶች የማክሸፍ፣ የአገር ክብርና ሉዓላዊነትን የማስከበር ዲፕሎማሲ እውን ማድረግ ያስፈልጋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምንም እንኳ ገና 5 አመት ቢሆነውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንካሬን እየተላበሰ የሚሄድ ባህል እያዳበረ መጥቷል፡፡ በዚህ ሥርዓት የአገርን አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እውን ማድረግ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ከውጭ የሚመነጭ ግኡዝ ነገር ሳይሆን ከውስጥ የሚያብብ ስሜት ለመሆኑ የታየበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም፡፡
የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ መንግስቱ ባጎናጸፋቸው መብት የኃይማኖት እኩልነትና ነፃነት የተከበረላቸው ሲሆን፥ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት እንዲሁም የመንግስትና የሃማኖት ልዩነትም ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡ የፖለቲካ ስርዓቱ ዲሞክራሲውን እያጠናከረው ሲሄድ ዲሞክራሲው ደግሞ የክልሉን ልማት በሁሉም ዘርፎች እያረጋገጠ ነው፡፡ በፌደራል ስርዓቱ ጥላ ስር የተሰባሰቡ እነዚህ የአገሪቱ ህዝቦች የልማቱ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡

ገጠርንና ግብርናን ማዕከል በማድረግ የተቀረጸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችንና የተሻሉ የአሰራር ዘዴዎችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን በግል፣ በቤተሰብና በአካባቢ ደረጃ ማረጋገጥ አስችሏል፡፡ የግብርና ግብዓቶችንና አጠቃላይ የኤክስቴንሽን ስራዎችን በሚገባ ተግባራዊ ያደረጉ በርካታ አርሶ አደሮች ሀብትና እሴት በመፍጠር ከተራ አርሶ አደርነት ወደ ባለሀብትነት ጉዞ ጀመረዋል፡፡

በሀሳብ መር ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የህዝቡን የነቃ ተሳትፎ በማሳደግ መጠነ ሰፊ ድሎች ተመዝገበዋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የአገሩቱ መንግስት አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ፣ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና ማስፋፋያ ስራዎች በህበረተሰብ ተሳፎ መስራት መቻሉ ተመላክቷል፡፡

ከመዋዕለ ህፃናት እስከ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከኮሌጆች እስከ ዩኒቨርሰቲዎች የዜጎችን የመማር እና የአገሪቱን የተማረ የሰው ሀይል ፍላጎ ለማሟላት እየተሰራ ነው፡፡

በጤናው ዘርፍ በሽታን አክሞ የማዳን ፖሊሲ አቅጣጫና ትግበራ ውጤት እየተመዘገበበት ነው፡፡ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን በሁሉም አከባቢዎች ያለው ተሳትፎ እያደገ ሲሆን በየቀበሌው የጤና ኬላዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በስፋት በማሰማራት የህዝቡን ግንዛቤ ማሳደግ ተችሏል፡፡

እንደየአካባቢው የህዝቡን ቁጥር መሰረት ያደረጉ የጤና ተቋማት ባላቸው አቅም ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ሲሆን፥ ከጤና ጣቢያ እስከ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለአገሪቱ ህዝብ የጤና ህክምና አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡

በተለያዩ የማህበራዊ ልማት ስራዎቻችን የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ፣ የማዕድ ማጋራት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እምርታ የታየባቸው ናቸው፡፡

የመብራት፣ የስልክና ሌሎችም የመገናኛ አውታሮች በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተስፋፍተዋል፡፡

ዜጎች በህገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን መደራጀት መብት ተጠቅመው በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም በተለያዩ የስራ እድል ፈጠራዎች ተሰማርተው ጥሪት በመቋጠርና ሀብትና እሴት ከማፍራት ባለፈ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን በማቅረብ የኢንዱስተሪ ሽግግር ሂደቱን እያቀላጠፉ ነው፡፡ በቋጠሩት ጥሪት፣ ሀብትና ገንዘብ ዛሬ በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ተሰማርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እየጠቀሙ ነው፡፡

በአገሪቱ ከተሞች ለዘመናት በስፋት ይስተዋሉ የነበሩ እጅግ ስር የሰደዱ የስራ አጥነት፣ የድህነትና ህዝቡን ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቀረፋቸው ከተሞች በከፍተኛ የለውጥ ጉዞ ላይ ናቸው፡፡ የነዋሪውን ህይወት የሚያሻሽሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ የከተማውን ህብረተሰብ የለውጡ ትሩፋት ተቋዳሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

የፌደራል ስርዓቱ ለህዝቦች ብልጽግናና ለኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት ሆኖ ቢቀጥልም በፖለቲካ እና ሐገረ-መንግስት የማፅናት ስራ ላይ አሁንም የሚንጸባረቀው ጽንፈኝነት፣ ነጠላ ትርክት፣ የተዛቡ ትርክቶች ጥለውት ያለፉት ጠባሳ፣ ጦርነት ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የተጓዘባቸው ልማትና የዲሞክራሲ ሂደት፥ እልህ አስጨራሽ፣ አስተዋይነት የተሞላበት፣ የፖለቲካ ትግል የተንጸባረቀበትና ከድህነት ጋር መሪር የሆነ ፍልሚያ የታየበት ነው፡፡ የዲሞክራሲ ትግሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣበት ሆኗል፡፡ አሁንም የትግሉ ኃይሎችና ትግሉ ብዙ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ከመላው የአገሪቱ ህዝብ ጋር፥ በጋራ በመሆን ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ በፓርቲውና በሀገሪቱ ህዝቦች እጣ ፈንታ ላይ ተስፋ የሚያሳጡ ሟርቶች ቢስተጋቡም አሁን ግን የባለብዙ ተስፈኞች ምድር መፍጠር ተችሏል፡፡ ዲሞክራሲ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በመፈጠሩ ለኢኮኖሚው እድገት አስተማማኝ መሰረት ጥሏል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ለአገራችን ህዝቦች አንድነትና ውስጣዊ ትስስር እንዲሁም ለጋራ ዓላማ ከመቼውም ጊዜ በላይ፥ በላቀ ደረጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል ፓርቲ ሲሆን፥ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው በሁሉም መሰረታዊ የእድገት አማራጮች ማሰሪያ ትሩፋት እንዲሆን ይተጋል፡፡