የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ በትብብር መስራት እንደሚገባ የኢፌዲሪ ስራና ክህሎት ሚኒስትር አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከስልጠና ባሻገር በየአካባቢው ያሉ እምቅ ፀጋዎችን ወደ ሀብት በመቀየር በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ በትብብር መስራት እንደሚገባ የኢፌዲሪ ስራና ክህሎት ሚኒስትር አስታውቋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተባባሪ ባለድርሻ አካላት የተመራ ልዑካን ቡድን የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስራ እንቅስቃሴ ሂደት ጎብኝቷል።
ጉብኝቱን የመሩት በኢፌዲሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ፤ በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን መነሻ በማድረግ የተቋማትን የስራ እንቅስቃሴ፣ የክህሎት ልማት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደቶችን መቃኘት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ጉብኝቱ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
በየአካባቢው ያሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ያሏቸውን እምቅ ፀጋዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ በሀገር ኢኮኖሚ መሻሻል ላይ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው ኮሌጁ በክህሎት ልማትና አምራቾችን ወደ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ የጀመራቸውን ተግባራት በላቀ ሁኔታ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የሆሳዕና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን የሆኑት አቶ አወል ሸንጎ በበኩላቸው፤ ኮሌጁ ከባለፉት ጊዜያት ጀምሮ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን በማፍራት የአካባቢን ችግር መቅረፍ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎችን ተደራሽ በማድረግና በሌሎች መስኮችም የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
የተቋሙን የውስጥ ገቢ በማሳደግ ከመንግሥት ጥገኝነት ለማላቀቅ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ አወል በተለይም በግብርና፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በጨረቃ ጨርቅና በልዩ ልዩ ዘርፎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ አምራቾችን ወደ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ በማሻገር አበክሮ እየሰራ ነው ብለዋል።
በጉብኝቱ የተካፈሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እና የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ዶቼ በጋራ በሰጡት አስተያየት፤ ኮሌጁ የተቋሙን ዲጅታላይዜሽን ስርዓት በማዘመን ከስልጠና ባሻገር ወደ ተግባር በመለወጥ ሂደትና ምቹና ሳቢ ገጽታ ከመፍጠር ጋር በተያያዘ እያሳየ ባለው የስራ እቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ይህንንም አጠናክሮ በማስቀጠልና በማስፋፋት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት መጎልበት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ሁሉም መረባረብ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ጤና ጣቢያው እየሰጠ ባለው አገልግሎት መደሰታቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ
የሰላምና የመከባበር ባህልን ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባ ተገለጸ