በፕሪሚዬርሊጉ ሳውዝሃምተን ከሊቨርፑል እና ኤፕስዊች ታውን ከማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ይጫወታሉ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ 12ኛ ሳምንት በዛሬው ዕለትም መካሄዱን ሲቀጥል ሳውዝሃምተን ከሊቨርፑል እንዲሁም ኤፕስዊች ታውን ከማንቸስተር ዩናይትድ ይጫወታሉ።
ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሳውዝሃምተን በሴንት ሜሪ ስታዲየም የሊጉን ሊቨርፑልን ያስተናግዳል።
ሊቨርፑል በሊጉ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች 9ኙን በማሸነፍ በ28 ነጥብ የሊጉ መሪ ሲሆን ሳውዝሃምተን በበኩሉ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች በተቃራኒው 9 ጨዋታዎችን በመሸነፍ በ4 ነጥብ 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሊቨርፑል የዛሬውን ጨዋታ መርታት የሚችል ከሆነ ከተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት 8 በማድረስ መሪነቱን ሊያጠናክር ይችላል።
በሊቨርፑል በኩል ሃርቬ ኤሊዮት እና የመስመር ተከላካዩ ኮነር ብራድሊ ከጉዳት ማገገማቸው ሲገለፅ አሊሰን ቤከር፣ ዲያጎ ጆታ፣ አሌክሳንደር አርኖልድ እና ፌዴሪኮ ቼዛ ግን በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ እንደማይሰለፉ ተነግሯል።
በሳውዝሃምፕተን በኩል የቀድሞ የአርሰናል ግብ ጠባቂ አሮን ራምስፌልድ ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ተገልጿል።
ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ አዲስ አዳጊው ኤፕስዊች ታውን ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው ያስተናግዳል።
በዚህ ጨዋታ የ39 ዓመቱ ወጣት አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ማንቸስተር ዩናይትድን እየመሩ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ሲያካሂዱ የኤፕስዊች ታውኑ አሰልጣኝ ኬራን ማኬና የቀድሞ ክለባቸውን ይገጥማሉ።
ኬራን ማኬና ከዚህ ቀደም በትያትር ኦፍ ድሪምስ ለ5 ዓመታት ምክትል አሰልጣኝ ሆነው መስራታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ክለቦች ከ22 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዛሬው ዕለት ይገናኛሉ።
በፖርትማን ሮድ ስታዲየም በሚካሄደው ጨዋታ በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ለረጅም ወራት በጉዳት ከሜዳ ርቀው የቆዩት ሉክ ሾው ፣ ታይሬል ማላሲያ እና ሌኒ ዮሮ ልምምድ መስራት መጀመራቸው ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ በሙሉቀን ባሳ
More Stories
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 6ኛ ዙር መርሐግብር 9 ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ
ሩድ ቫኔስትሮይ የሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ ሆኖ በይፋ ተሾመ
ሊቨርፑልና ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ ታላቅ ጨዋታን ዛሬ ምሽት ያካሂዳሉ