ኮሌጁ በመደበኛና የማታ መርሃ-ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመረቀ

‎ኮሌጁ በመደበኛና የማታ መርሃ-ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመረቀ

‎ሀዋሳ፡ ሕዳር 27/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዲላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመደበኛና የማታ መርሃ-ግብር ያሰለጠናቸውን 2 መቶ 52 ተማሪዎችን አስመርቋል።

‎ኮሌጁ በዛሬው ዕለት ያስመረቃቸው ተማሪዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በ3 የስልጠና ዘርፎች 9 በሚሆኑ የሙያ መስኮች ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸውን የዲላ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን የሆኑን አቶ ሀብታሙ አለማየሁ አስረድተዋል፡፡

‎ኮሌጁ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች አምራች ዜጋን እያፈራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ በቀጣይም ተቋሙን ለሰልጣኞች ምቹና ሳቢ በማድረግ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

‎በሰልጣኞች ምረቃ መርሃ-ግብር የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) ተቋሙ በከተማው የኮሪደር ልማት ሥራው እንዲፋጠን የተማረ የሰው ኃይልም ሆነ ግብዓት በማቅረብ ለከተማው ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥራና ክህሎት ምክትል ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ሙያ ህዝብና ሀገራቸውን እንዲያገለግሉና በተማሩት ሙያ ሥራ በመፍጠር ውጤታማ ለመሆን እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

‎የያነጋገርናቸው ተመራቂዎች በበኩላቸው፤ በስልጠና ቆይታቸው ያካበቱትን ክህሎት ራሳቸውን፣ ህዝቡንና ሀገርን ለመለወጥ እንደሚጠቀሙበት አንስተው፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የተግባር ተኮር ስልጠና ማዕከል በመሆናቸው ሥራ ለማግኘትም ሆነ ፈጥሮ ለመሥራት አመቺ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‎ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን