ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች በማህበር ተደራጅተው በመስራት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ገለፀ

ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች በማህበር ተደራጅተው በመስራት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስልጤ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ገለፀ

በዞኑ አልቾ ወረዳ በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች የተሰሩ የልማት ስራዎች የመስክ ምልክታ ተካሂዷል።

በመስክ ምልከታው ወቅት የተገኙት የስልጤ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊና የገጠር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብድልመነን ሀጂ ሁሴን እንደገለፁት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ነው።

በዞኑ ያሉ የአካባቢ ፀጋዎችን በመጠቀም በግብርና፣ በማንፋክቸሪንግ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በሌሎች የልማት ዘርፎች ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በመስራት ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት በዞኑ ለ70 ሺ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ14 ሺህ ወጣቶች በከተማ እንዲሁም ለ16 ሺህ ወጣቶች ደግሞ በገጠር የተለያዩ የስራ ዘርፎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በወጣቱ ዘንድ የነበረውን በስደት ሰርቶ የመለወጥ እሳቤን በመቀየር ወጣቶች የአካባቢያቸውን ፀጋ ተጠቅመው በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱንም ገልፀዋል።

በዞኑ አልቾ ውሪሮ ወረዳ ወጣቶች በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው በተሳተፉባቸው የተለያዩ የልማት ዘርፎች ያስመዘገቡት ውጤት ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑንም ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው ወቅት የተገኙት የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ መህድያ ሀሰን በበኩላቸው ወጣቶችን ከስራ አጥነት በማላቀቅና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ያስቀመጠውን የኢንዱስትሪ ሽግግር እውን ለማድረግ ወጣቶች ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በማምረት እና ለሌሎች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸው እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች ጊዜያቸውንና እውቀታቸውን ተጠቅመው ራሳቸውን እና ማህበረሰቡን በሚለውጡ የስራ መስኮች በመደራጀት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በስልጤ ዞን የአልቾ ዉሪሮ ወረዳ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሀ ፍቅሬ በበኩላቸው፤ በወረዳው በዘንድሮ በጀት ዓመት ለ6 ሺህ 2 መቶ 24 ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን ባለው 2 ሺህ 6 መቶ 17 ወጣቶች በ1 መቶ 72 ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው በወረዳው በተለያዩ ቀበሌያት በማህበር በተደራጁ ወጣቶች የተሰሩ የልማት ስራዎች አመርቂ ውጤት የተመዘገበባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው በኩተሬ እና በቃዋቆቶ ክላስተር በዶሮ እርባታ፣ በእንስሳት ማደለብ፣ በበጋ መስኖ እንዲሁም በገብስና ስንዴ ብዜት ልማት የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ምልከታ ተካሂዷል፡፡

በወረዳው በተለያዩ ማህበራት ተደራጅተው በተለያዩ ስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች በበኩላቸው በአካባቢያቸው የሚገኙ ፀጋዎችን በመጠቀም የመንግስትን ስራ ከመጠበቅና በሀገር ሰርቶ መለወጥን በማሰብ በግብርና፣ በከብት እርባታ፣ በማንፋክቸሪንግ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች በመሰማራት ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ሙጅብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን