ሀዋሳ፡ ሕዳር 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ሊያሻሽሉ የሚችሉ አሠራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የ2017 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማና ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ የሚመክር መድረክ በገደብ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ፥ በሁሉም አደረጃጀቶች የአመለካከትና የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በተሠሩ ሥራዎች ውጤት ማስገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የህብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ሊያሻሽሉ የሚችሉ አሠራሮች ተዘርግተው እየተሠሩ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በተወሰኑ ወረዳዎች የተጀመሩ ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደልና አዳዲስ ችግኞችን የመተካት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በዞኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቁን ድርሻ የያዘው የእንሰት ምርት መሆኑን የገለጹት አቶ አበባየሁ፤ የእንሰትና የቡና ተከላ ሥራዎች ላይ በንቅናቄ መልክ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን በመደገፍ በዶሮ፣ ወተትና ሌሎች ዘርፎች የተገኘውን ውጤት ለማስፋፋት ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በማህበራዊ መሠረት የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀቶችን በማጠናከር የፓርቲውን ህልውና ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የደረሰውን የቡና ምርት በጥራት የማሰባሰብ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት አቶ አበባየሁ፤ ህብረተሰቡ በበጋ ወቅት ከቡና ሽያጭና ከቀን ሥራ ያገኘውን ገንዘብ በአልባሌ ቦታ ከማባከን ቁጠባን መሠረት በማድረግ ኑሮውን በአግባቡ መምራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የገደብ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ምትኩ፥ ወረዳው የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የገጠር ቀበሌያትን ትስስር ለማጠናከር የመንገድና ሌሎች የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫ ጽ/ቤቶች የሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሸፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በትራፊክ አደጋ ምክንያት በዜጎችና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሚዲያ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የኑሮ ጫናን ለመቀነስ አጋዥ መሆናቸውን የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ገለፀ
ወጣቱ በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ በመሆን ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ እንዲያመጣ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ