ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በክህሎትና ሙያ ዘርፍ ብቁ የሆነ ተማሪ ለማፍራት የአዲሱ ትምህርት ፕሮግራም ከፍተኛ ፋይዳ አለው – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ

ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በክህሎትና ሙያ ዘርፍ ብቁ የሆነ ተማሪ ለማፍራት የአዲሱ ትምህርት ፕሮግራም ከፍተኛ ፋይዳ አለው – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በክህሎትና ሙያ ዘርፍም ብቁ የሆነ ተማሪን ለማፍራት የአዲሱ ትምህርት ፕሮግራም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለፀ።

የ2017 ሥራና ቴክኒክ ትምህርት ማስጀመሪያ ፕሮግራም በኮንታ ዞን ጪዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሂዷል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሥራና ቴክኒክ ትምህርት ማስጀመሪያ ፕሮግራም በኮንታ ዞን ጪዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተካሂዷል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና ስርዓተ ትምህርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አባተ ኡቃ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ አሰራሮች እየተዘረጉ መሆኑን አንስተው ከነዚህም አንዱ ከቀለም ባለፈ ተማሪዎች የሙያ እውቀትን ይዘው እንዲወጡ የሚያስችል ፕሮግራም ነው ብለዋል።

በዚህም እንደ ሀገር በ8 መስኮች ባሉ 40 በሚያህሉ ሙያዎች በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሥራ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

በክልሉም በ12 ሙያዎች ስልጠና ለመስጠት 11 ሺህ 4 መቶ የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ተመዝግበው ወደ ሥራ መገባቱንም አቶ አባቴ ጠቅሰዋል።የሥራና ቴክኒክ ትምህርቱ በተለይም በአካባቢው ፀጋ ላይ ትኩረት እንደሚደረግበትም አሳስበዋል።

ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን ስራ ፈጣሪ ዜጋን ለመፍጠር ተማሪዎች በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰለጥኑ ማድረግ  ስራ አጥነትን ለመቀነስ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የጪዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዓለሙ ኮቾ ገልፀዋል።

የኮንታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አበራ እንደገለፁትም ከዚህ ቀደም የነበረው የትምህርት ፖሊሲ በቀለም ትምህርት ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ ከ12ኛ ክፍል በኋላ በተለይም ወደ ዩኒቨርሲቲ ያልገቡ ተማሪዎች ላይ ሥራአጥነት እንዲበራከት አድርጓል።

አዲሱ የትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎች የሙያ ስልጠና ወስደው የሥራ ዕድልም ይዘው እንዲወጡ የሚያስችል በመሆኑ ይህን ተግባር ለማሳካት የበኩላቸውን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በጪዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም አሁን ላይ በኮምፒውተር ጥገናና ጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሥራ ላይ ትምህርት መሰጠት መጀመሩን ጠቁመዋል።

የኮንታ ዞን ምክትል አስተዳደርና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድምአገኘሁ ወጁ ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት ፕሮግራም ክፍተቶችን ለማረም የክህሎትና ሥራ ላይ ትምህርት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዘርፉ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በማስጀመሪያ መርሃግብሩ የክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊን ጨምሮ የትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያዎች የኮንታ ዞንና የጭዳ ከተማ አስተዳደር አመራር አካላት የተገኙት ሲሆን በጪዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዘርፉ እየሰጠ ያለውን ትምህርት ጎብኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን