ሀዋሳ፡ ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ በክልል ደረጃ የሚከናወን የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ የውይይትና ለሐገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች መረጣ መድረክ በይፋ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ደማቅ ዕሴቶች ባለቤት ብትሆንም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ያለመግባባት እና መሠረታዊ የሀሳብ ልዩነቶች እሴቶቿን እየሸረሸሩት መጥተዋል ነው ያሉት።
እነዚህ መሠረታዊ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ሰፋፊ የሕዝብ መድረኮችን በማካሄድ ችግሮቹን ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ ጥረቶችን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ዶክተር ዮናስ፥ ኮሚሽኑ የሦስት ዓመት እስትራቴጂያዊ ዕቅድ በማዘጋጀት እየሠራ ነው ብለዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት የዛሬውን ሳያካትት በምክክሩ ሂደት 932 ወረዳዎች ተሳታፊ ሆነዋል ያሉት ኮምሽነሩ፥ በ7 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በስኬት መጠናቀቁን አመላክተዋል፡፡
ጉባኤው በ32 ብሔረሰቦች መናገሻ በሆነችው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ፣ የውይይትና ለሐገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች መረጣ የማድረጊያ መድረክ መሆኑን ጠቁመው፥ ከ12 የክልሉ ዞኖችና ከ96 ወረዳዎች ከ3 ሺህ 800 በላይ ተሳታፊዎች ለ6 ተከታታይ ቀናት የሚሳተፉ እንደሆነ ያወሱት ዶ/ር ዮናስ ምክክሩ በይፋ መከፈቱን አብስረዋል።
ተሳታፊዎቹ ቃለ መሀላ በመፈጸም ጉባኤውን ጀምረዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የቡርጂ ዞን ምክር ቤት አቶ ትንሳኤ ዮሐንስ ወጌ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ
የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠርን ጉዳይ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ እየሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ተገልጋዩን ለማርካት እየሰራ መሆኑን የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ