የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ግምታቸው ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ለሚዲያ አገልግሎት የሚውሉ ግምታቸው ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
የጂንካ ዩኒቨርስቲ የልማትና አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አለሙ አይለቴ በድጋፉ ወቅት እንደገለፁት፤ የጂንካ ዩኒቨርስቲ ተቋሙን በስልጠና በመደገፍ እየሰራ ካለው ሥራ ባሻገር የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የሚዲያውን ሥራ በውጤታማነት እንዲያከናውን ታስቦ የተደረገ ነው።
ደረጃቸውን የጠበቁ ለሚዲያ ቴክኖሎጂ ሥራ የሚውሉ ዘመናዊ ኮምፒተሮች፣ ዲጅታል የኃይል መቆጣጠሪያ ዩ.ፒ.ኤስ እና ሌሎችም ድጋፍ የተደረጉ ሲሆን አጠቃላይ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው እንደሆነም ገልፀዋል።
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዋስ ኢቲሳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርስቲው ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ከዚህ ቀደምም ለሚዲያ ባለሙያዎችና በዙሪያው ላሉ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሙሉ ወጪ ችለው ሰልጠና በማመቻቸት የደገፈ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ከዩኒቨርስቲው ጋር በመቀናጀት ለሚዲያ ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ቀደም ብሎ የመግባቢያ ሰምምነት በተፈራረሙት መሠረት እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል።
ዩኒቨርስቲው የሚያደርገውን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ በቀጣይም እንዲያጠናክር ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፉ በተቋሙ ያሉ የግብዓት እጥረቶችን ከመፍታት ባሻገር የሚሰሩ ዜናና ፕሮግራሞች በተሻለ ጥራት እንዲደርስ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የይዘት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ፍቃዱ ግዲ እና የሚዲያ ቴክኖሎጂ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ በፀጋው ታመነ ናቸው።
ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከቻይና ገጠር ልማት ፋውንዴሽንና ከሐመር ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረጉ
በሲዳማ ክልል ለተገኘው ሰላም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነበር – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ
የአራቱም ክልሎች የጋራ ሃብት የሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሄደ