258ኛው የኤልክላሲኮ ደርቢ ዛሬ ምሽት ይካሄዳል
በስፔን ላሊጋ 11ኛ ሳምንት ተጠባቂው የኤልክላሲኮ ደርቢ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በኤል ሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ስታዲየም ይካሄዳል።
በ3 ነጥብ ልዩነት በደረጃ ሰንጠረዡ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች በሳምንቱ አጋማሽ በሻምፒዮንስ ሊጉ የጀርመን ክለቦችን በማሸነፍ ድልን በተቀዳጁ በቀናት ልዩነት ምሽት ላይ ይገናኛሉ።
በጀርመናዊው አሰልጣኝ ሃንሲ ፍሊክ የሚመራው ባርሴሎና በላሊጋው ካከናወናቸው 10 ጨዋታዎች 9ኙን በማሸነፍ በ27 ነጥብ 1ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ጥሩ ጅማሮን በማድረግ ላይ ይገኛል።
በእነዚህ ጨዋታዎች የካታላኑ ክለብ 33 ጎሎችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ አሳርፏል። በአንድ ጨዋታ በአማካይ 3.3 ጎል ያስቆጥራል እንደ ማለት ነው።
በአዲሱ የውድድር ዓመት በላሊጋው ሽንፈትን ካላስተናገዱ ሁለት ክለቦች አንዱ የሆነው ሪያል ማድሪድ በ42 ተከታታይ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ሎስብላንኮዎቹ በምሽቱ ጨዋታ ሳይሸነፉ ከሜዳ የሚወጡ ከሆነ ያለመሸነፍ ጉዟቸውን 43 በማድረስ በ2017-18 የውድድር ዓመት በባርሴሎና ከተያዘው ክብረወሰን ጋር መጋራት ይችላሉ።
የባርሴሎናው አሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ እና የሪያል ማድሪዱ የፊት መስመር ተጫዋች ክሊያን ምባፔ የመጀመሪያቸውን የኤልክላሲኮ ደርቢ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑ ይሆናል።
ሁለቱ ክለቦች እ.ኤ.አ ከ1902 አንስቶ እስካሁን 257 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሪያል ማድሪድ 106 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ባርሴሎና 100 ጊዜ ሲያሸንፍ በ51 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በኤልክላሲኮ ደርቢ ሊዮኔል ሜሲ 26 ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚው ተጫዋች ነው።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና አልፍሬዶ ዴስቲፋኖ 18 ጎሎችን በማስቆጠር ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 6ለ1 አሸነፈ
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ የምስክር ወረቀት ተሰጠው
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች