አርሶ አደሩ የደረሱ ምርቶችን በወቅቱ መሰብሰብ እንዳለበት ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኣሪ ዞን በተያዘው የመኸር ወቅት የደረሱ የሰብል ምርቶች እየጣለ ባለው ወቅታዊ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስባቸው አርሶ አደሩ ምርት እንዲሰበስብ የዞኑ ግብርና መምሪያ አሳስቧል።
በዞኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ቀድሞ የደረሱ የጤፍና ሌሎች የመኸር ሰብሎች እየተሰበሰቡ ይገኛሉ።
በዞኑ በባኮ ደውላ ኣሪ ወረዳ የባያሞር ቀበሌ የጤፍ ምርት እየሰበሰቡ አግኝተን ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ዮሴፍ በርጊ፣ ገበያው ማሎ እና ሌሎችም እንዳሉት፤ አሁኑ ላይ እየጣለ ያለው ዝናብ የደረሰው ምርታቸው ላይ ጉዳታ እንዳያደርስ ቤተሰብን በማስተባበር እየሰበሰቡ ይገኛሉ።
አርሶ አደሮቹ አክለው እየጣለ ያለው ዝናብ ጤፍን ጨምሮ በሌሎች ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንዳለ ጠቁመው ሌሎችም ምርታቸውን በወቅቱ በመሰብሰብና ጎርፍን ከማሳቸው በመቀልበስ ከጉዳት እንዲታደጉ ጠይቀዋል፡፡
የባካ ደውላ ኣሪ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ በረከት ወንድሙ፤ በወረዳው በመኸር ምርት 4 ሺህ 4 መቶ 5 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብል ምርቶች በመሸፈን ከ220 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገንባቱን ጠቁመዋል፡፡
አርሶ አደሩ አሁን ላይ እየጣለ ያለው ወቅታዊ ዝናብ ምርታቸውን እንዳይጎዳ የደረሱ የመኸር ሰብል ምርት እንዲሰበስቡ ጥሪ ያቀረቡት በኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ዘርፍና ምክትል መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ፍቅሬ ሚልክያስ፤ በዞኑ በተያዘው የመኸር ወቅት 28 ሺህ 3 መቶ 70 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 87 ሄክታር መሬት በጤፍ ምርት ተሸፍኗል ብለዋል።
አቶ ፍቅሬ አክለው የጤፍ ምርት በቀላሉ በዝናብ ሊጎዳ ስለሚችል በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች የደረሱ የጤፍ ምርቶችን አርሶ አደሩ በተደራጀ ሁኔታ ምርት እንዲሰበስብ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ የሺእመቤት ዋሴ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ