ሀዋሳ፡ መስከረም 25/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ከሲ ፎር ኢክራፍ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን ወርክ ሾፕ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚሠራ ታስክ ፎርስ በማቋቋም ተጠናቋል።
ለአከባቢ መራቆት የህዝብና የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻ ቦታ መስፋፋትና የደን መሬት ወረራ ዋነኛ ምክንያቶች ናችው ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም በጋራ ተረባርቦ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአከባቢ ጥበቃ፣ በግብርና ልማትና ሥራ ፈጠራ ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን ከሲፎር ኢክራፍ ጋር በመሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረጋቸውንና ሁሉም አከባቢ የማስፋት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የእርሻ ቦታ ባለመኖር ምክንያት ለማስፋት ተብሎ የደን መጨፍጨፍና የምርታማነት ችግር በውይይቱ የተነሱ ለአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ያሉት የሲ ፎር ኢክራፍ ፕሮጀክት ኃላፊና የጥምር እርሻ ዓለምአቀፍ ተመራማሪ ዶ/ር አስቴር ገ/ክርስቶስ ይሄን ለመቅረፍ ተቀናጅቶ መሥራት ብቸኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል።
በውይይቱ ለተነሱ ዋና ዋና ችግሮች የመፍትሔው ባለቤት የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ናቸው ያሉት ተመራማሪዋ ተቀናጅቶ በመሥራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል።
በቀጣይ ባለው የመሬት አጠቃቀም ካርታ በማዘጋጀት ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ተመራማሪዋ በተለይ ሚዲያ ባለው አማራጭ ሁሉ ማገዝ እንደሚገባው ጠይቀዋል።
ከፕሮጀክቱ ጋር ብዝሃ-ሕይወትን ለመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚሠሩ ሥራዎች በጥናትና ምርምር እንዲሁም ለሴቶችች፣ ለወጣቶችና ለአርሶ አደሮች በአቅም ግንባታ አብሮ እንደሚሰራ የገለጹት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና የብዝሃ-ሕይወት አያያዝ መምህር ጌታሁን ሀይሌ (ዶ/ር) በጋራ ከፕሮጀክቱ ጋር መሥራታቸው ለራሳቸው፣ ለተማሪዎቻቸውና ለማህበረሰቡ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል።
የአግሮ ኢኮሎጂ ባለሙያና የውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ጢባ ማልዴ እና ቅድስት ብርሃኑ በበኩላቸው ተፈጥሮን ለመጠበቅና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥምር እርሻን ሞዴል አድርጎ በማስቀጠል በሁሉም አካባቢ ለማስፋት በቅንጅት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የማህበረሰብ ተወካዮች፣ አባ ገዳዎች፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ ከክልል ከዞንና ወረዳ የመጡ ባለድርሻ አካላት በወርክ ሾፑ የተሳተፉ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚሠራ ታስክ ፎርስ በማቋቋም ተጠናቋል።
ዘጋቢ: ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ