ሀዋሳ፡ መስከረም 25/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንስቲትዩት የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2017 ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ አካሂዷል።
ዶክተር ብሩክ ከድር የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተቋሙ በባለፈው ዓመት በዘርፉ ጥራት ያለውን ተግባር ለማከናወን ብዙ ጥረቶችን እያደረገ መቆየቱን ጠቁመው ከመደበኛ ስራ ጎን ለጎን የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማካሄድ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል።
በ2017 የሀገራችንን ቴክኒክና ሙያ ይበልጥ ሊያሻሽሉ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በአጽንኦት የመከረ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ተደራሽነቱን ከማስፋት ባሻገር ጥራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ቴክኒክና ሙያ ስራን ከቴክኖሎጂ ነጥሎ ማየት አይቻልም ያሉት ዶ/ር ብሩክ ተቋሙ በዘርፉ በተሰሩ ስራዎች የ”አይ ኤስ ኦ” እስታንደርድ ተሸላሚ የሆነበት ዓመት መሆኑን አንስተው የሀገሪቱን ቴክኖሎጂ በማዘመን አደጉ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጅነር ሰለሞን ፈርሻ በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ጠቁመው ምንም እንኳ በሀገራችን ዘርፉ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም በእድሜው ልክ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ አላበረከተም ብለዋል።
በአሁን ጊዜ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚሰሩ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውንም ኢንጅነር ሰለሞን አክለው ገልፀዋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ተቋሙ የስልጠና፣ የአቅም ግምባታ ና የክህሎት ልማት ተግባራትን እየከወነ የሚገኝ ተቋም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በዘርፉ የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መድረኩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ውይይቱ በዘንድሮ ዓመት “ዓመተ ልህቀት 2” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ እንስቲትዩት አመራሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ የስልጠና ክፍል ኃላፊዎችና በየክልሉ ያሉ የሳተላይት ኮሌጅ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ