የመስቀል በዓል ሲከበር እርስ በርስ በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመስቀል በዓል ሲከበር ያለው ከሌለው በመተጋገዝና እርስ በርስ በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ።

የሃይማኖት አባቶቹ በዓሉን በማስመልከት የመልካም ምኞት መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

የመስቀል በዓል በአይሁዶች ተቀብሮ የነበረ የክርስቶስ መስቀል መገኘትን ምክንያት በማድረግ የወቅቱ አማኞች በዓል ሰርተው ለመብል የሚሆን በማዘጋጀት በጋራ ደስታ ያከበሩበት አብነት ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊና የሆሳዕና ደብረ ኢዮር ቅዱስ ራጉኤል ወመርቆርዎስ ደብር አስተዳዳሪ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር ክፍል ኃላፊና የሆሳዕና ደብረ መዊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም አስተዳዳሪ መጋቤ ትፍስሕት ቀሲስ ዳዊት አብርሃም ገልፀዋል።

በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ባህላዊ ይዘቶች ያለው ቢሆንም ሃይማኖታዊ መሰረት ያለው ስለመሆኑም የሃይማኖት አባቶቹ አክለው ተናግረዋል።

ታዲያ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት ያለው ከሌለው ጋር በመተሳሰብ በፍቅርና በአብሮነት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ አክለዉም በዓሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የፍቅርና የደስታ እንዲሆን በመመኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን