ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተከተሉት የሰከነ የፖለቲካ ትግል ስልት በአርዓያነት የሚወሰድ መሆኑ ተገለጸ

በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በኮለኔል በዛብህ ጴጥሮስ መታሰቢያ አደባባይ በተካሄደው ሀዘን የመግለጽና ሻማ የማብራት ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡

የሀዲያ ዞን ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከተማው ነዋሪዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ፣ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የሀዲያ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር በፈቃዱ ገ/ሃና እንዳሉት የፕሮፌሰሩ ህልፈት ለዞኑና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥልቅ ሀዘን የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ በቆዩባቸው ዓመታት ለትውልድ የሚሻገር አኩሪ አሻራ ማሳረፋቸውንም አውስተዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተለመደ መልኩ የሰላማዊና የስክነት ፖለቲካ አካሄድ ብቻ በመከተል ለዲሞክራሲ መጎልበት የበኩላቸውን የተወጡ ጉምቱ ፖለቲከኛ እንደነበሩ አንስተው የአሁኑ ትውልድ አርዓያነታቸውን ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል ።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ በበኩላቸው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ  ላለፉት ረጅም ዓመታት ለሚውዱት ሀገራቸው ያላቸውን አቅም ሳይሰስቱ በትምህርትና በምርምር በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲሁም በኃላፊነት በመሩባቸው የመንግሥት ስራዎች ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት ያገለገሉ የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

ከተማ አስተዳደሩ ህልፈታቸው ከተሰማ ጊዜ አንስቶ  የዞኑ ህዝብና መላው ወዳጆች ሀዘኑን በአንድነት እንዲገልጽ  ለማስቻል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው ከማለዳ አንስቶ በሀዲያ ባህላዊ የለቅሶ ስነ ስርዓት ጥልቅ የተሰማውን ሀዘን በአደባባይ መግለጹን አስታውቀዋል፡፡

የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ  ፕሮፌሰሩ ለሀገር ያበረከቷቸው ሥራዎች ለመጪው ትውልድ በተገቢው ተሰንዶ መተላለፍ ያለበት በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል ።

በዕለቱ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት በህልፈታቸው መሪር ሀዘን እንደተሰማቸው ገልፀው ሆኖም ለሀገር ያበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ እየተዘከረ የሚኖር ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን