በ2016 ያገጠመው መጻሕፍት እጥረት በተያዘው ትምህርት ዘመን ችግሩ እንዲፈታ የቡርጂ ዞን ተማሪዎች ጠየቁ

የዞኑ ትምህርት መምሪያ በበኩሉ የመጽሀፍት እጥረት ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የአየለ ገልዶ ትምህርት ቤት የ7ኛና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሱብዓት ቆሬ እና ሜሮን መለሰ እንዲሁም የአክያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ጉያቱ አየለ በ2016 ትምህርት ዘመን ውስን መጽሐፍት በቤተ መጻሕፍት ብቻ ይገኝ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ውስን መጽሀፍት ቀድሞ ከሚያገኙ ውስን ተማሪዎች ውጭ ለሌሎች የሚዳረስ ባለመሆኑ በውጤታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አንስተዋል፡፡

የቡርጂ ዞን ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርትና ትግበራ ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ ሣሊም አበበ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በ2017 ዓ.ም የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው የመጽሐፍ እጥረት ችግርን ለመፍታት ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋር እየሰሩ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

በመጻሕፍት ህትመት ላይ ትኩረት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ከ4ኛ-6ኛ እና ከ9ኛ-12ኛ ክፍል 34 ሺህ 748 መጻሕፍት ታትመው ወደ ትምህርት ቤት ለማሰራጨት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከወዲሁ አስፈላጊ ግብአትን በማሟላት ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ዮሴፍ ቶልኬ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን