ሀዋሳ፡ መስከረም 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጉራጌ ብሄር ተወላጆች ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ለመስቀል በዓል ሲገቡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ዜጎች በስፋት የሚጋብዙበትና የሚሳተፉበት በመሆኑ ለማህበረሰባዊ ቱሪዝም ትልቅ ማሳያ መሆኑን የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለፀ።
መምሪያው በዘርፉ የገጠሩን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግም እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በመስቀል በዓል ወቅት በተለያዩ የጉራጌ አካባቢዎች የብሄሩ ተወላጅ ያልሆኑ እና በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ጭምር ወዳጃዊ ግብዣ ተደርጎላቸው ማየት እየተለመደ መጥቷል።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ እንደገለፁት የመስቀል ክብረበዓል ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ ባለፈ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት እሴቶች የሚታዩበት እንዲሁም የጋብቻ ስርዓት የሚፈፀምበት ነው።
”የዴጝ” እና ”የገሚያ” እሳት ወይም የልጆች እና የአባቶች ደመራ ስነ-ስርዓት ልዩ ገፅታ፣ ተሰባስቦ በየወጉ የሚቀርቡ የምግብ አይነቶች እና አመጋገብ እንዲሁም ሌሎችም ትእይንቶች ብዙ ጎብኚዎች እንዲሳቡ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
እነዚህ ቱሪስቶች ይበልጥ ከተወላጁ ጋር በመግባባት ወደ ጉራጌ አካባቢ የሚገቡ ሲሆን ”እኔን ለመስቀል በዓል ወደ ጉራጌ ማን ይውሰደኝ” የሚሉ ሰዎች በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር አስጎብኚዎች በማሳተፍ ወደ ተግባር መገባቱም ሀላፊዋ ገልጸዋል።
ለአብነትም ራይድ ዘ ቱር ላይፍ፣ ዳይነስቲ ቱር እና ሌሎች የሀገር ውስጥ አስጎብኚዎች በመስቀል በዓል በተለያዩ ጉራጌ አካባቢዎች ከጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ከሌሎችም ሀገራት እና ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን ይዘው እንደሚመጡም ተናግረዋል።
በየቤቱ እና ጀፎሮ ላይ አለፍ ሲልም በቤተክርስትያን በመገኘት የመስቀል ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስርአት እንደሚመለከቱም አውስተዋል። በዚህም ደስተኛ በመሆናቸው ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱም አመላክተዋል።
በዚህም የእግር ጉዞ፣ የባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል በመገልገል እንደሚዘዋወሩና ጊዜያዊ ድንኳን ጭምር በተለያዩ ቦታዎች እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል። ይህም ለጎብኚው ማስታወሻ የሚሆኑ የተለያዩ የእደ ጥበብ ውጤቶች ለማዘጋጀት እና ለመሸጥ ያስችላል ብለዋል።
ማህበረሰባችንም ከማብላት እና ከማጠጣት ጎን ለጎን ተፈጥሮአዊ እና ባህላዊ የቱሪስት መዳረሻዎቻችንን ማስጎብኘት ይገባዋል ነው ያሉት።
ቱሪስቶቹ በእንግድነት ከመቀበል እና በክብር ከማስተናገድ ባለፈ ለተሰጠው አገልግሎት ተመጣጣኝ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል አሰራር መዘርጋቱንም ወ/ሮ መሰረት ተናግረዋል።
ይበልጥ በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆንና የጉራጌ መገለጫ የሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመገንባት እና የጎብኚዎች ቆይታ ለማራዘም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚያነሳሳም ሀላፊዋ አስረድተዋል።
በመጨረሻም ሀላፊዋ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለብርሃነ መስቀሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ